


የጉራፈረዳ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት በህገወጥ መንገድ ተከማችቶ የነበረ ቤንዚንና ናፍጣ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
በጉራፈረዳ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ኩራቱ በላቸው እንደገለፁት በወረዳዉ በኩጃ ቀበሌ ላይ፣ በተለምዶ አሸዋ ዳጌት ተብሎ በሚጠራው መንደር ሰሞኑን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ባደረገው ፍተሻ 194 በርሜል ህገወጥ የነዳጅ ምርት መያዙን ተናግረዋል።
129 በርሜል ቤንዝል እና 65 በርሜል ናፍጣ ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በህገወጥ መንገድ ነዳጁን ያከማቸውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልፀዋል።
ፖሊስ ከዚህ ህገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን፣ የህግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ኩራቱ ህገወጥነትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም፣ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል ሲል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ዘግቧል።
