




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን የሰው ተኮር ተግባራት ላይ እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም ለገሠ እንደተናገሩት ከመደበኛ የመንግስት ስራ ጎንለጎን የፓርቲያችን መገለጫ በሆነው ሰው ተኮር ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት በክልሉ ባሉ ከተሞች ላይ በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውን አስታውቀዋል ።
በዚህም ቀደም ሲል በተርጫ፣ሚዛንና ቦንጋ የደሀ ደሀ ቤት ገንብቶ ከመስጠት በተጨማሪ ለአቅመ ደካማ ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ማሟላትና ሌሎች የሰው ተኮር ተግባራትን ስናከናውን ቆይተናል ብለዋል።
ዘንድሮም በማሻ ከተማ የአቅመ ደካማ ቤት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ግንባታ ማስጀመራቸውን አስታውቀው በሁለት ወራት ውስጥ ጨርሶ ለማስረከብ የማስጀመሪያ ፕሮግራም አካሂደዋል።
የሸካ ዞን ሴቶች ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ከበደም እንደ ሀገር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የሰው ተኮር ተግባራት ላይ ትኩረት ተሰጠው እየተሰራ እንደምገኝ ገልፆ በዞኑ ውስጥ በምገኙ መዋቅሮች ላይ የደሀ ደሀ ቤት የመገንባት ስራ ከክልሉ ቢሮዎች ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።
የማሻ ከተማ ከንቲባ አቶ አንዱአለም ጌታቸው በበኩላቸው የብልፅግና ፓርቲ ባስቀመጠው የሰው ተኮር አቅጣጫ መሠረት የክልሉ ውሃ ቢሮ በተለያዩ ከተሞች የደሀ ደሀ ቤቶች ለማስገንባት በያዘው ውጥን የማሻ ከተማን ተጠቋሚ በማድረጉ አመስግነዋል ።
የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ደሴ አደሞ በበኩላቸው ቀደም ሲል የሚኖሩበት ቤት ለመኖር ምቹ ባለመሆኑ ለተለያዩ በሽታዎች ሲጋለጡ መቆየታቸውን ገልፀው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል ሲል ማሻ ኤፍ ኤም ዘግቧል።
