የኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን በአጭር ጊዜ የሚያሳልጥ ወሳኝ እርምጃ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

Spread the love

የኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን በአጭር ጊዜ የሚያሳልጥ ወሳኝ እርምጃ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

የኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን በአጭር ጊዜ የሚያሳልጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌዴራል መንግስትን የ2018 ዓ.ም ዋና ዋና የልማት ዕቅዶች አቅርበዋል።

በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግርም፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ብቻ አይደለም ብለዋል።

ይልቁንስ የሀገራችን የፖለቲካ ተራክቦት ኢኮኖሚና የማህበራዊ ህይወትን የሚቀይር ወሳኝ የሽግግር ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የዲጂታል ቴክኖሎጂን በማስፋት፣ የመረጃ ልውውጥን በማቀላጠፍና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን በአጭር ጊዜ እውን የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።

በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመትም ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል አገልግሎቶች በዲጂታል ማዕቀፍ የሚሰጡበትን ምኅዳር የማሳለጥ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የዲጂታል ዘርፍ ለሌሎች ዘርፎች አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራበትም አስገንዝበዋል።

በ2025 የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ አመርቂ ውጤቶች አንዲመዘገቡ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተመዘገበውን ውጤት ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የዲጂታል ትግበራውም ለህብረተሰቡ የቀረበና እንግልትን የሚቀነስ አገልግሎት በመዘርጋት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥርዓትም በላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማዘመን በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ አፈፃጸም በማጎልበት የመረጃ ሉዓላዊነት አቅም እንደሚገነባ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *