




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2017 በጀት ዓመት በዩኒሴፍ ድጋፍ የተሰሩ ፕሮጄክቶች የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በፕሮግራሙ የታቀፉ የ8 ሴክተሮች አፈጻጸም ሪፖርት ቀርበው ግምገማ የተደረገባቸዉ ሲሆን በቀጣይ መስተካከል የሚገባቸው ሀሳቦች ላይ ዉይይት ተደርጎ ከመግባባትም ተደርሷል፡፡
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ እንዳሉት፤በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ በዩኒሴፍ ፕሮግራም ገንዘብ ድጋፍ በተሰሩ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
የክልሉን ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በዩኒሴፍ (UNICEF)በጀት ድጋፍ የተተገበሩ ፕሮጀክቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸዉ በቁርጠኝነት መምራትና መተግባር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ዓላማ የሚመደበዉን ዉስን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የቢሮ ምክትልና የመንግስታት ትብብርና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ዓለሙ በበኩላቸዉ፣በጀት ዓመቱ ለፕሮጄክቶች ስራ ስኬታማነት የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል በመደረጉ ዉጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት የሚተገበሩ ተግባራትን በተሻለ መልኩ በመፈጸም የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የቅንጅት ስራዎች እንዲጠናከሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የዩኒሴፍ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑተ አቶ አጼ ቴዎድሮስ ድርጅቱ መንግስት መድረስ የማይችልባቸዉ ቦታዎች ላይ አስፈላጊዉን ድጋፍ በማድረግ
በ2017 በጀት ዓመት 2መቶ30 ሚሊዮን ብር በክልሉ በሚገኙት 8 ተቋማት በማከፋፈል የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ በዩኒሴፍ ገንዘብ ድጋፍ የሚተገበሩ ፕሮግራሞች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በመሆናቸዉ ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉም የሚጠበቅባቸዉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸዉን አስረድተዋል።
በካሳሁን አሰፋ
