የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም(FSRP) ጋር በመሆን በግብርናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የሚደገፍ የጎጀብ እና ታርጫ ምርምር ንዑስ ጣቢያዎች የመስኖ ጥናትና ዲዛይን ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በቦንጋ አካሂደዋል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) ከተቋሙ ጋር በመቀናጀት በክልሉ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ዘርፌ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ የምርምር ቴክኖሎጂን ማመንጨትና ምንጭ ቴክኖሎጅን ማባዛት፣ የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ እና የምርምር አቅም የመገንባት ተግባርን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

በተሰሩ ስራዎች ከምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመቀናጀት በግብርና ቴክኖሎጂ ማመንጨት ላይ በሰብል፣ በእንስሳት እርባታ፣ በፈጥሮ እና በአግሮ ኢኮኖሚክስ 13 ቴክኖሎጂዎችን ማመንጨት መቻሉን አንስተዋል።

ምንጭ ቴክኖሎጂ ከማባዛት አንጻር 989 ኩንታል ዘር ፣ 40ሺ በላይ የቡና ችግኝ ተዘጋጅቶ መላኩን እንዲሁም 6940 የአቮካዶ ችግኞችን በኩታ ገጠም ለማስተከል ተዘጋጅቶ መላኩን አብራርተዋል።

የግብርና ቴክኖሎጂን ከማስተዋወቅ 9 የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም 390 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን በማንሳት በ11 የግብርና ቴክኖሎጂዎች 772 አርሶ አደሮችን በክላስተር በተመሠረተ ሰርቶ ማሣያ በማሳተፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

በከተማ ግብርና የተመረጡ 4 ቴክኖሎጂዎችን ብርቱካን ሆርቲካልቸር እርሻ፣ በምግብ ማቀነባበሪያ እና አመጋገብ፣የሃይድሮፖኒክ እርሻ ለእንስሳት አረንጓዴ መኖ እና የዶሮ እርባታ ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አክሏል።

በምርምር አቅም ግንባታ 68 የሚጠጉ ተመራማሪዎችን በተለያዩ የሶፍትዌር ፓኬጆች ላይ ስልጠና እና ለምርምር ዳይሬክተሮች ከሌሎች ክልሎች የልምድ ልውውጥ ማድረግ መቻቸቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በመስኖ ዘርፍ የሚታዩ ጉድለቶችን በጋራ በማረም፣ ዘርፉን በማስፋፋት፣ የአካባቢው ተጽዕኖን በአግባቡ በማስተዳደርና የውሃ አጠቃቀምን ሳይንሳዊ በማድረግ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚገባ ተናግሯል ።

በፌደራል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ መከላከል ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ አብረሃም አበበ በክልሉ በፕሮግራሙ የመጡ ውጤቶችን በመስኖ ዘርፍ ለመድገም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል ።

በመስኖ ዲዛይን ጥናት ዙሪያ የአካባቢው ተጽዕኖ ግምገማ ሰነድ የክልሉን ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ስርዓት ማጠናከራሪያ ማኔጀር በሆኑት በዶ/ር አብይ ገ/ሚካኤል ለተሳታዎቹ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ ላይ የመስኖ ልማት ስራው በግብርናው ዘርፍ ቴክኖሎጂን በማመንጨት፣ በማባዛትና በማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግም ባሻገር የስራ ዕድልን እንደሚፈጥር ያነሱት ተሳታፊዎች የጥናቱ የአካባቢው ተጽዕኖ ቀድሞ በባለድርሻ አካላት መገምገም በጥናቱ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን እንደ ግብዓት የተነሱ ጉዳዮችን በማካተት ለተግባራዊነቱ የባለድርሻ አካላት መናበብና ቅንጅት እንደሚሻ ተነስቷል።

በመድረኩ ላይ ከፌደራል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ኤክስፐርቶች፣ የቦንጋ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተሮች፣ የግንቦ ወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ አልሚ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *