የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማሸጋገር እንደሚገባ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ ያልተነኩ ባህላዊ ቅርሶቹን፣ ታሪካዊ ሀብቶቹንና ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻዎቹን ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ለመቀየር የሚያስችል ጉባኤ በታርጫ ከተማ ተጀመረ።

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ያዘጋጀው ይህ መድረክ፣ ያለፈውን ዓመት አፈፃፀም በመገምገም የቀጣዩን ዘመን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፣ የቢሮው ዋነኛ ግብ የክልሉን ህዝቦች ልዩ የሆኑ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ታሪኮች እና የስፖርት ተሰጥኦዎች በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን አስምረውበታል።

“ባህል የማንነታችን መስታወት ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጫችንና የማህበራዊ ትስስራችን ማጠናከሪያ ነው” ያሉት አቶ ፋንታሁን፣ ባህል ግጭቶችን በመከላከል ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመገንባት እና የህዝቡን የስነ-ልቦና አንድነት ለማጠንከር ያለውን ሚና አብራርተዋል።

ኃላፊው የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በተመለከተ ሲናገሩም፣ “ክልላችን የተንበሸበሸበትን የቱሪዝም መስህቦች በአግባቡ በማልማት፣ ህዝቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ የእያንዳንዳችን ድርሻ ነው” ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም ጤናማ፣ ምርታማና በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ስፖርት ያለውን ወሳኝ ሚና የገለጹት አቶ ፋንታሁን፣ በክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተጀመሩ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በመጨረሻም፣ “የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ስማቸውን በበጎ የሚያስጠራ አሻራ ጥለው ማለፍ አለባቸው” ሲሉ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በታርጫ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው በዚህ ጉባኤ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም፣ የ2018 ዕቅድ እና የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ይደረግበታል። በዝግጅቱ ላይ ከስድስቱም ዞኖች እና ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የዘርፉ ኃላፊዎችና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።

ጉባኤው ያለፉትን ስራዎች ከመገምገም ባሻገር፣ በቀጣይ የክልሉን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፎች የሚጫወቱትን ሚና የሚያጠናክር አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *