ለመንገድ ልማት ፕሮጀክት የሚመደቡ በጀቶች ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ግልጽና ወጥ የግዥና ፋይናንስ አዋጅ እና መመሪያ መከተል ያስፈልጋል ፦ኢንጂነር አብዲዩ መኮንን

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የመንገዶች ባለስልጣን በግዥና ፋይናንስ አዋጆችና መመሪያዎች ላይ ለመሥሪያ ቤቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ነዉ።

የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራአስኪያጅ ኢ/ር አብዲዩ መኮንን ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት፤ለመንገድ ልማት ፕሮጀክት የሚመደቡ በጀቶች ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ግልጽና ወጥ የግዥና ፋይናንስ አዋጅ እና መመሪያ መከተል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ኢንጂነሩ በባለስልጣኑ የሚከናወኑ በተለይም ነዳጅ፣ማሽነሪዎችና ሌሎች መለዋወጫ ግብዓቶች ግዥ በሚፈጸምበት እና በሚስተዳደርበት ወቅት በክልሉ መንግስት ከግዥ ዝግጅት እስከ አፈጻጸም እንዲሁም የፋይናንስ አሰራር ወጥና ግልጽ ለማድረግ የወጡ አዋጆችና መመሪያዎችን መከተል እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።

በክልሉ መንግስት ለመንገድ ልማት ፕሮጀክት የሚመደበው ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የስልጠናው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ስልጣኖች በተገቢው መከታተልና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ደግሞ የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራአስኪያጅ እና የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ አየለ ናቸው።

የክልሉ ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን የግዥ ስልጠናና ንብረት ቁጥጥርና ክትትል ሙያዊ ድጋፍ ዳይረክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደጎል ሰለሞን ለመሥሪያ ቤቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች በግዥና ፋይናንስ አዋጅ እና መመሪያ ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ስልጠናው የግዥ ሥርዓት ግልጽ፣ቀልጣፋ፣ፍትሃዊ፣አድሎ የሌለበት ቁጣባና ውጤታማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እንዲሁም በህጋዊነት ኦዲት የሚገኙ ነቀፌታዎችን መቀነስ የሚያስችል እንደሆነም አቶ ደጎል በወቅቱ ተናግረዋል።

በስልጠናው የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮች እና ባለሙያዎች፣ የሶስቱ ዲስትርክት ሥራአስኪያጆች፣ የማኔጅመንት አባላትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *