
በተለያዩ ምክንያቶች ለጊዜው ተቋርጦ የቆየውን የጎሬ – ማሻ – ቴፒ መንገድ ፕሮጀክት ወደ ግንባታ ለመመለስ የሚያስችሉ ጉዳዮች እየታዩ ነው፡፡
141 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የጎሬ – ማሻ – ቴፒ መንገድ ፕሮጀክት በዓለም-አቀፉ የሥራ ተቋራጭ ሃይንዳይ ዴቨሎፕመንት ካምፓኒ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት ግንባታው ሲከናወን እንደቆየ ይታወቃል።
ኾኖም የግንባታው አጠቃላይ አፈጻጸም 62 በመቶ ከደረሰ በኋላ ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች በወቅቱ አለመቀረፋቸውን እንዲሁም የግንባታ ውል ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የነበሩ አለመግባባቶችን በምክንያትነት በማንሳት የሥራ ተቋራጩ ግንባታውን ለጊዜው አቋርጧል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱን በፋይናንስ የሚደግፈው የኮሪያው ኤግዚም ባንክ ከፍተኛ አመራሮች በቀጣይ ቀናት አዲስ አበባ የሚገቡ ሲኾን፤ ግንባታው ዳግም በሚመለስበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሚመክሩ ይሆናል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዳይስተጓጎል አስፈላጊ የጥገና ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የመንገድ ግንባታው ዳግም እስኪጀመር ድረስም የጥገና ሥራው የሚቀጥል ይሆናል።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ኦሮሚያን እና ጋምቤላን በኢሉ አባቦር በኩል እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን በሸካ ዞን በኩል በቅርበት በማስተሳሰር ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያበረክት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ስድስት ወረዳዎች እና ከ15 በላይ ቀበሌዎችን በቅርበት በማገናኘት ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር የሚያጠናክር ነው፡፡
መረጃው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ነው።
