የህብረተሰቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የአስፈጻሚ አካላት ተግባር የመከታተል እና መደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች አስታወቁ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የየዘርፉ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2018 ዓ.ም የ1ኛ ሩብ ዓመት የአስፈፃሚ አካላት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ 5 የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በየዘርፋቸው ተከፋፍለው የየራሳቸውን ሪፖርት በመገምገም የቀጣይ ስራዎች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ከ1ኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መልስ በክልሉ ቋሚ ኮሚቴዎች የመስክ ምልከታ እንደሚያካሄድም ተጠቁሟል።

የህግ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ አምሳሌ ንጋቱ ፣በህብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው የሚነሱ ጉዳዮችን ለመፍታት ለአስፈፃሚው አካል የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት በጀት ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ የክልሉ በጀት የፋይናንስ አሰራር ስርዓቱን ጠብቆ ወደ ታች እንድወርድ መድረግ፣የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ፣ሀብትን ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የኦዲት ጅምር ስራዎች እንዲሁም የግዢ ስርዓቱን ለማጠናከር የነበሩ አፈጻጸሞች በጥንካሬ እንደተገመገሙ ጠቅሰው በጉድለት የታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

በክልሉ ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተረፈ ሀብተማርያም በግምገማው መድረኩ የአስፈፃሚ አካላት የዕቅድ አፈጻጸም በሚገባ መልኩ መገምገሙን፣በድክመት የታዩ ነጥቦች ላይ ውይይት መደረጉን እና የቀጣይ አቅጣጫ መስቀመጥ መቻሉ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የሚያስችል ተግባር እንደሆነ አመላካች ነው ብለዋል።

በምክር ቤቱ የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አዲስምዕራፍ ዓለሙ የምክር ቤት አባላት የህብረተሰቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማደረግ የአስፈጻሚ አካላትን ተግባር መከታተል እና መደገፍ ይጠበቅባቸዋል በማለት ተናግረዋል።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *