




ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የአርሶ አደር መር የተፈጥሮ ማገገሚያ ዘዴ(FMNR) ፕሮግራም የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና 2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ አካኺዷል።
FMNR በክልል ደረጃ በ 5 ዓመታት ውስጥ 299 ሺህ 545 ሄክታር የተራቆቱ መሬትን መልሰው እንዲያግም ለመስራት አቅደው እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት 32 ሺህ 686 ሄ/ር መሬት በግለሰብ፣ በግጦሽ እና በጋራ መሬት ዘርፎች ማልማት መቻሉ ተመላክቷል።
በግምገማው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ: ፕሮግራሙ በክልሉ ውስጥ በመሬት ጥበቃ እና ልማት ልይ የተሠማሩትን ፕሮጀክቶች በማቀናጀት የዕውቀት ሽግግር እያደረገ ነው ብለዋል።
አዲሱ ትውልድ ተፈጥሮን የሚጠብቅ እንዲሆን የተቀናጀ ንቅናቄ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ወብሸት ይኸን ዓላማ ለማሳለጥ ፕሮግራሙ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ላይ የአካባቢ ጥበቃ ክበቦችን ተጠቅሞ የችግኝ አዘገጃጀት ስራዎችን በመደገፍ ለአረንጓዴ አሻራ ስራ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ የተጎዱ መሬቶችን ለይተው ከሰውና እንስሳት ንኪኪ ውጭ ካደረገ በኃላ መልሰው ማልማት ነው ያሉት የፕሮራሙ አስተባባሪ አቶ አለሙ ዳካ: አርሶ አደሮችን በማሰልጠንና በማሳተፍ መሬታቸውን አልምተው እንዲጠቀሙ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
መሬት ከሰውና ከእንስሳት ከንኪኪ ከጸዳ በኃላ ከአፈር ውስጥ የሚበቅሉ፣ ከጉቶ የሚበቅሉና ሌሎች ከስርና በተከላ የሚበቅሉ ችግኞችን በራሱ በአርሶ አደር በመምራት ውጤት እየታየ መሆኑን አክለዋል።
የማገገሚያ ተግባራት በሁሉም አደረጃጀቶች በኩል ይሰርጻል ያሉት አስተባባሪው ማህበረሰቡን ለማንቃት መምህራንን በማሰልጠን ለትምህርት ማህበረሰቡ ከማሳወቅ እስከ ስርዓተ ትምህርት ድረስ የሚካተትበት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
መንግስታዊ ያልሆኑ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ አለሙ: መንግስታዊ ኢኒሼቲቮችን በማጠናከር ከባቢ አየሩ ለመጪው ትውልድ ምቹ ሆነው እንዲሸጋገር FMNR እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሮግራሙ የተራቆቱ መሬትን በሚያለማበት ወቅት ማህበራትን በማደራጀት እና መነሻ ድጋፍ በመስጠት በበግ ማሞከት፣ በዶሮ እርባታና እርሻ ስራዎች ከ 7 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ለስራ ዕድል ፈጠራ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑም ተመላክቷል።
በመጨረሻም የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በየዞኑ ቀርበው ከተወያዩ በኃላ የአተገባባር አቅጣጫ አስቀምጠው አጠናቋል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
