የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው – የዓለም ጤና ድርጅት

Spread the love

ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ያከናወነቻቸው ተግባራት የሚደነቁና በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

በዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ቺሳካት እንዳሉት ኢትዮጵያ የዜጎቿን የጤና አገልግሎት ጥራት ተደራሽነት ለማስፋት ያከናወነችው ተግባር የሚደነቅና በተሞክሮነት የሚወሰድ ነው።

ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ቺሳካት ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ ትልቅ እምርታ አስመዝግባለች።

በኢትዮጵያ ዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም በሀገር ውስጥ መድኃኒት በማምረት ላይ ስኬታማ ስራ እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ደህንነቱ የተረጋገጠ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ለድንገተኛ በሽታዎች ምላሽ ለመስጠት የሚሰራውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተለይም አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልጉ በሽታዎች እና ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ስኬታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመድሃኒት ማምረቻ ማዕከል እንድትሆን እገዛ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *