ኢትዮጵያ በካካዎ ምርት የላቀ ውጤት ማምጣት የሚያስችል አቅም አላት

Spread the love

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ በካካዎ ምርት የላቀ ውጤት ማምጣት የሚያስችል አቅም አላት አለ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በውጭ ገበያ ተፈላጊነት ያላቸው እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ሰብሎችን ጨምሮ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎች ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውንና በኢትዮጵያ የማይታወቀውን የካካዎ ሰብል ለማላመድ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ በኢንስቲትዩቱ የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አማካኝነት የካካዎ ሰብል ምርምር እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ቸኮሌትን ጨምሮ የተለያዩ ጣፋጭ የምግብ ሸቀጦችን ለማምረት በግብዓትነት የሚያገለግለውን ካካዎ በኢትዮጵያ ለማምረት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም እንዳለ መታየቱን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ አየር ንብረት ምቹ የሆነ የካካዎ ዝርያ በምርምር መፍለቁን ጠቅሰው፤ በሰርቶ ማሳያ ደረጃ ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚቻል መረጋገጡን ጠቁመዋል።

ይህንን ተሞክሮ ወደ አርሶ አደሩ እና ሌሎች አምራቾች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ በስፋት እየተሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል።

የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ከ32 ሺህ በላይ የካካዎ ችግኝ አዘጋጅቶ በ2017 ዓ.ም የክረምት ወቅት ለአርሶ አደሩ ማቅረቡ ይታወሳል።

የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የሆኑት ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ካሜሩን እና ናይጄሪያ በካካዎ አምራችነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ይታወቃሉ ሲል ኤፍኤም ሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *