




የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ንግድን ለማሳለጥና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ለስኬቱ በጋራ መስራት እንደሚገባ የጅማ እና አምቦ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን ማለታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ተዘግቶባት መኖር አትችልም፤ ለጎረቤቶቻችን መናገር የምንፈልገው ኢትዮጵያ ስታድግ ለቀጣናው ልማት ምንጭ ትሆናለች፤ የምንፈልገው በትብብር ማደግ ነው፤ በመሆኑም የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው በማለት አጽንኦት ሰጥተውም ተናግረዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን መኮንን ቦጋለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሲሳካ በቀጣናው ያላትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖን የሚያጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህር በር ጥያቄው በኢትዮጵያ የተወጠኑ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ መሰረት በመጣል የሀገሪቱን የማንሰራራት ጉዞ እንደሚያፋጥንም ጠቁመዋል።
የኢኮኖሚ እድገት የተለያዩ ስራዎች ጥምር ውጤት መሆኑን አንስተው የባህር በርም የዚሁ ዋነኛ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንቨስትመንትን በመሳብና በማነቃቃት ሀገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸው፤ ለስኬታማነቱ ሁላችንም መረባረብ ይገባል ብለዋል።
የባህር በር ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር አካል መሆኑን ያነሱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ደመላሽ መንግስቱ (ዶ/ር) ናቸው።
መንግስት ጉዳዩን የህዝብ አጀንዳ ከማድረግ ባለፈ በጋራ መልማት ላይ መሰረት ያደረግ ዲፕሎማሲን መከተሉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
አጀንዳው ከውጤት እንዲደርስም የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አውስተው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እውን መሆን በቀጣናው ያላትን ሁለንተናዊ አበርክቶ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
በርካታ የህዝብ ቁጥር ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ህጋዊም ሆነ ታሪካዊ አመክንዮ እንዳለው እስረድተዋል።
በተመሳሳይ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ጥያቄ እና በዓለም አቀፍ ህግም የሚደገፍ መሰረታዊ መብት ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ኃብት መምህር ታደለ መላኩ (ዶ/ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን በተሻለ መልኩ የሚያሳድግ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ መሆኑንም ተናግረዋል።
የባህር በር ጥያቄው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መገንባት እንድትችል እና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ነጋሳ ፉፋ
ጥያቄው ለውጤት እንዲበቃ አንድነትን በማጠናከር ከመንግስት ጎን መሆን እንደሚገባ አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
