








የግብርና ሚኒስቴር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ስርዓተ-ፆታና ኤች አይ ቪ ኤድስ ሜንስትሪምንግ ጋር በመተባበር ለክልሉ ግብርና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች፤መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ፕሮግራሞች በስርዓተ-ፆታና ማህበራዊ ጉዳይ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማስፋት የሚያስችል የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የግብርና ልማት ዕቅድ ጀንደር ስትራቴጂ ሰነድ በግብርና ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያ በሆኑት በአቶ አብዱልጀሉል ናስር ቅርቦ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩም የክልሉ ግብርና ቢሮ የ2018 ዓም ጠቋሚ ዕቅዱን መሰረት በማድረግ በስርዓተ-ጾታና ማህበራዊ ጉዳዮች አንጻር ያለዉ ዕቅድ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ገነት አብደላ እንዳሉት፣በሀገሪቱ ትልቅ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ግብርና በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሁሉንም ዜጋ በእኩል ማሳተፍና ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ ዕዉን ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሴቶችን ተሳትፎና ፍታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚስችል የጀንደር ስትራቴጂ ዕቅዱን መከለስና ውጤታማ እንዲሆን እስከ ወረዳ ድረስ ያለው ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መፈጸም እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የስርዓተ-ጾታ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መዋቅራዊ ለዉጥ ማምጣት አስፈላጊ እንደሆነም አክለዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ልዩ አመካሪና የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሀንስ መላኩ በበኩላቸዉ ፣ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደረጉ የግብርና ኢኒሼቲቭ ስራዎች መልካም ልምዶችን ወደ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ፍታዊ ተጠቃሚነት ለማሳካት በሁሉም የልማት ዕቅድ ላይ አካታችን መሰረት በማደረግ ለትግበራዉም መተጋገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር፣ ሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ችግር ያለባቸዉ ወገኖችን ተጠቃሚና ተሳታፊ ከማድረግ አንጻር የታየውን ወጤት ለማስፋትና ክፍተቶችን ለመቅረፍ የጋራ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዉ እነዚህ ዜጎች ወደ ግብርናው ዘርፍ በስፋት ገብተው እንዲያለሙ ማገዝና ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ገልጸው፣በሀገራችን በግብርናው ዘርፍ በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የድጋፍ አሰጣጡን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ተሳታፊዎቹም በሰጡት አስተያየት የዉይይት መድረኩ በሴቶች ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጾ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ተናግረው፣የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚጠበቅባቸዉን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
በካሳሁን አሰፋ
