




የሾዶ ፏፏቴ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣በካፋ ዞን፣ጨታ ወረዳ የሚገኝ ድንቅ የቱሪዝም መስህብ ነው።
ድንቅ ተፈጥሮ የተቸረው የጨረታ ወረዳ የበርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት ነው።
በወረዳው አጠቃላይ ከ34 ባላይ የተለዩ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች መኖራቸውን ከወረዳው ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ባለ-ሶስት ደረጃው የሾዶ ፏፏቴ ከእነዚህ ውብ የአከባቢው የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች አንዱ ሲሆን ከዞኑ ርዕሰ ከተማ ቦንጋ በ67 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኝ ሲሆን፣
ከጨታ ወረዳ ርዕሰ ከተማ ከሻማ የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ በማድረግ በዱባ ቀበሌ፣ ቆንባ መንደር ላይ ይህን ክረምት ከበጋ የፍሰት መጠኑንና ወዘናው የማይነጥፈውን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት መመልከት ይቻላል።
የሾዶ ፏፏቴ ከጫፉ ውሃው ወደ ታች፣ መሬት እስከደረሰበት ባለ 3/ሶስት/ አስገራሚ የፍስት እርከኖችን ሲኖሩት፣ አከባቢው ደግሞ በእድሜ ጠገብ ዛፎችና ነፋሻማ አየር የታጀበ መኾኑ ልዩ ያደርገዋል።
የፏፏቴ ቁመት በግምት ከ50 ሜትር በላይ፥ ስፋቱ ደግሞ ከ12 ሜትር እንደሚበልጥ ከወረዳው ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሾዶ ፏፏቴ አካባቢው በጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን የተከበበ በመሆኑ ለቱሪዝም መስህብነት ማራኪ የሆነ ስፍራ ቢሆንም፤ እንደ አካባቢው መስህብነት አጥጋቢ በሆነ መልኩ ለቱሪስት መዳረሻ አልኾነም።
በመኾኑም የባለድርሻ አካላት ይህንን ድንቅ የቱሪዝም ሀብት በተገቢው የማስተዋወቅና የማልማት ሥራ ቢሰሩ ከቱሪዝም የብዝሀ ዘርፍ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ድርሻ ማሳደግ ይቻላል የሚለው የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት ነው።
በዕድገቱ በዛብህ
