የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ደረጃ በደረጃ ከመንግስት በሚቀመጠዉ አቅጣጫና አሠራር ሥርዓት ለመመለስ እንደሚሰራ ተመላከተ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ክልል ዓቀፍ የመልካም አስተዳደር ቅሬታና አቤቱታ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂደዋል።

በውይይቱ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የቅሬታ አቤቱታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ ኬና በቅሬታ አቤቱታ ጉዳዮች ዙሪያ የተዘጋጀ ሠነድ አቅርበው ምክክር ተደርጓል።

በመድረኩ የተገኙ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የቅሬታና አቤቱታ ማጣራት ዴስክ ኃላፊ አቶ ሽዋንግዛዉ ማሞ እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ክልሎችን ያካተተና በክልሎች እሰከ ወረዳ መዋቅር ድረስ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ተቋማዊ ፎረም ተቋቁመው ቅሬታዎች እንዲፈቱ እየተደረገ ይገኛል።

በተቋቋመው ፎረም መሠረት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለረዥም ዓመታት ተዳፍነው የቆዩ ውስብስብ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች እየተደመጡ ምላሽ እያገኙ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በፌደራል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጀምሮ በሁሉም ክልሎች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የህዝቡ መልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን አዳምጦ መፍታት እና የህዝቡ እርካታ ማሳደግ የሚያስችሉ ተገልጋይ ተኮር ዳሳሳዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል ኃላፊዉ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተረፈ ዘዉዴ እንደገለጹት፦ ከህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት በየዘርፉ የተጀማመሩ የልማት ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላሉ።

በክልሉ በየደረጃዉ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን እስከህዝቡ ወርደው በማዳመጥ ደረጃ በደረጃ ከመንግስት በሚቀመጠዉ አቅጣጫና አሠራር ሥርዓት መሠረት ለመመለስ እንደሚሰራም አቶ ተረፌ ዘዉዴ ገልጸዋል።

በክልሉ በቅሬታ አቀባበልና አቤቱታ አፈታት ዙሪያ ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም አደረጃጀትና ቅንጅታዊ አሠራሮችን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ተደርገው ሊሠራ እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት አንስተዋል።

በዚህም በፌደራል፣ በክልል፣ በዞን እንዲሁም በተዋረድ ባሉ መዋቅሮች መመለስ የሚገቡ መልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን መፍታት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *