


የወተትና ስጋ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማዳቀል ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የወተትና ሥጋ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች የማዳቀል ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ላሞችን ለማዳቀል ዕቅድ ተይዞ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በፈሳሽ ናይትሮጅን አማካኝነት የወተትና ሥጋ ምርታማነትን ማሳደግ የሚችል የተሻሻሉ ዝርያዎች እየተዳቀሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት በዓመት 500 ሺህ እንስሳት ይዳቀሉ እንደነበረ አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት 5 ሚሊዬን የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ላሞችን ለማዳቀል መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
በወተትና ሥጋ ምርታማነት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን በማንሳት፥ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች የምግብ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ካስጀመሩ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያንዳንዳቸው በሰዓት 30 ሊትር ፈሳሽ ናይትሮጅን የማምረቻ አቅም ያላቸው ማሽነሪዎች በተለያዩ ከተሞች ተተክለዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በግ፣ ፍየልና ሌሎች እንስሳትን ለማዳቀል የሚያገለግሉና በሰዓት 50 ሊትር ፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረት የሚችሉ ማሽነሪዎች በግዥ ሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከፈሳሽ ናይትሮጂን በተጨማሪ በኮርማ አባል ዘር የማዳቀል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤በቀጣይ የበግ፣ ፍየልና ሌሎች እንስሳትን ማዳቃል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
