ክልላዊ የአርሶ አደር የመስክ ላይ ትምህርት ቤት ተቋማዊ ማድረጊያ ፕሮግራም በጊምቦ ወረዳ ተካሄደ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአርሶ አደር የመስክ ላይ ትምህርት ቤት (FFS Institutionalisation) ተቋማዊ ማድረግያ ፕሮግራም በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ሃማኒ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የካፋ ዞን ግብርና ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ አማዴ የኤስ ኤን ቪ ፕሮጀክት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ በ6 ቀበሌዎች በአትክልትና ፍራፍሬ ወጣቶችና ሴቶችን በማደራጀት በርካታ ስራዎችን መስራቱን ገልፀዋል፡፡

በዞኑ በፕሮጀክቱ የተጀመሩ ተግባራትን ተቋማዊ በማድረግና ከመንግሥት ተግባራት ጋር በማቀናጀት አደረጃጀቶችን በማጠናከር አርሶ አደሮችን በማንቃት ወደ ስራ ለማስገባት ያለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ የሆርቲካልቸር ሰብሎች ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ገ/ሚካኤል፤ አርሶ አደር የመስክ ትምህርት ቤት የኤክስቴንሽን መንገድ መሆኑን ጠቅሰው ይህም እንደ ክልል በተለያዩ ድርጅቶች እየተሰራ መምጣቱንና ጥሩ ውጤት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህን ተግባር ተቋማዊ ለማድረግና ቀጣይነት እንዲኖረው እያንዳንዱ ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዲደግፉ ክልላዊ አቅጣጫ የተቀመጠ መሆኑንና ሰፊ እቅድ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ አክለውም በዚህ ዓመት በ24 ወረዳዎች 196 አርሶ አደር የመስክ ትምህርት ቤቶች እንደሚሰሩ እና ለዚህም በFSRP፣ በLLRP እና በPACT ፕሮጀክቶች ከ19 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልፀዋል፡፡

በዚህ ተግባር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ ዝርያዎችንና የአሰራር ዘዴዎች አርሶ አደሩ እራሱ ወደ ውሳኔ የሚመጠበት መመሪያ መድረክ በመሆኑ ሁሉም ኃላፊነት ወስዶ በመስራት ውጤታማ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከርያ (FSRP)ፕሮግራም ማነጀር አቶ ወንደሰን ሁሴን የኤስ ኤን ቪ ፕሮግራም ባላፉት ጊዜያት በአርሶ አደር መስክ ትምህርት ቤት ውጤታማ ተግባራትን ስያከናውን መቆየቱንና አሁን የቆይታ ጊዜውን በማጠናቀቁ የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ FSRP ፕሮጀክት ለስራው ውጤታማነት በበጀት የሚደግፍ መሆኑን አርሶ አደሩ በፕሮግራሙ ያገኘውን ተሞክሮ በማስቀጠል የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልል፣ የዞንና የወረደ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደ ክልል ተቋማዊ የተደረገው የአርሶ አደር የመስክ ላይ ትምህርት ቤት ቀጣይነት እንዲኖረውና ውጤት እንዲመጣ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ግንዛቤ የመፍጠር፣ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *