የሀገራችን የመልማትና የብልፅግና ጉዞ በልጆቿ አንድነትና መተባበር እውን ይሆናል:-ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን “ከጂኦስትራቴጂካዊ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ቃል ከዞን፣ ከወረዳና ከተማ አስተዳደር ለተወጣጡ ፖሊስ አመራሮችና አባላት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

በማጠቃለያው ላይ ተገኝተውመልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ሀገራችን ያለችበትን የፖለቲካ፣ኢኮኖሚያዊና ጂኦስትራቴጂካዊ ሁኔታን በጥልቀት በመረዳት ካለፈው በላቀ መልኩ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ መዘጋጀታችሁን በመረዳቴ ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል።

ሀገራችን የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ አመርቂ ድሎችን እያስመዘገበች ትገኛለች ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ የሀገራችንን ልማትና ዕድገት የማይወዱ ጠላቶች በእክ አዙር የውስጥ ባንዳዎችን ተጠቅመው የሀገራችንን ሠላምና ልማት ለማጓተት እየጣሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ የጸጥታና ፖሊስ መዋቅር እንደ ወትሮ ሴራቸውን እያመከነ እዚህ ደርሷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም የጠላቶቻችንን ሴራ በተሟላ መልኩ ለማክሸፍ አሁን በወሰዳችሁት ስልጠና መሠረት በእውቀትና ትጋት ለኢትዮጵያ አንድነትና ልማት መዘጋጀት አለባችሁ ብለዋል።

ህብረብሔራዊ አንድነቷና ሉዓላዊ ክብሯ የተጠበቀባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የፖሊስ ሀይል በላቀ ትጋት መስራት እንዳለበት ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ አሳስበዋል።

ሀገራችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ የመልማት መርህ ትከተላለች ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ የመልማት ፖሊሲ በመከተል ብሔራዊ ጥቅሟን አስከብራ ብልፅግናዋን በህዝቦቿ ትጋት ታረጋግጣለች ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በየአካባቢያቸው ጸጥታን የሚያናጉ፣ የህዝቦችን አንድነት የሚረብሹ፣ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር የሚያካሂዱ አካላትን ስርዓት የማስያዝ እንዲሁም ከኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ፖሊሲ ተገቢውን ሚና መወጣት እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የፖሊስ ስርዓትን ለማዘመንና ለማጠናከር ክልሉ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ነው ያሉት ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ባለን ጥቂት ሀብት ለፖሊስ ተጨማሪ አባላት ማሰልጠንና የነበሩት በተለያዩ ሙያ ስልጠናዎች የማጠናከር ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የክልሉን ህዝብ ክብር የሚመጥን ፓሊስ ተቋም ለማደራጀትም ክልላዊ ማርሽ ባንድ እያሰለጠንን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይን አብረን ለጋራ ሀገራችን ልማትና ብልፅግና የሚንሰራ ይሆናል ብለዋል።

በያዝነው በጀት ዓመት ሀገራዊ ምርጫ የሚደረግበት በመሆኑ ምቹ አውድ ለመፍጠር ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እና ምርጫው ፍትሐዊና ተዓማኒ እንዲሁም የሀገር ልማትን የሚያሳልጥ ምርጫ እንዲካኸድ የፖሊስ አባላት ሠላም የማስከበር ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *