የሚያለዩንና የሚያናቁሩንን ነጠላ ትርክቶች በመተው የጋራ የሚያደርጉንና ገዥ ትርክቶችን ማጽናት ይገባል ። ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሀመድ

Spread the love

“ሕብረብሔራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ” በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ ውይይት ተጠናቋል።

በቦንጋ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይቶች ከተሳታፊዎች አስተያየት እና ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ከቦንጋ ከተማና ከዙሪያ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በዞኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሆነው የሰነበቱ ምላሽ እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል ።

ከለውጡ ማግስት በዞኑ እየተስተዋሉ ያሉ ጅምር የልማት ስራዎች በዘላቂነት ለፍጻሜ እንዲበቁ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ችግር የአሁኑ ትውልድ ችግሮች አይደሉም ችግሮቹን ለመፍታት ደግሞ የአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅበትን ማድረግ ይገባዋል ሲሉም ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ያለፈው ትውልድ ችግሮችን በዛፍ ጥላ ስር ሆኖ ችግሮችን በመፍታት ሀገራችንን ለእኛ አስረክቧል ፤ ያሁኑ ትውልድ ድህነትን መዋጋት፣ከቴክኖሎጂ ጋር መዋሃድ የሚጠበቅበት እንጂ መገዳደል መገለጫን አይደለም ሲሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የዞኑ ህዝብ ሰላም ወዳድ ነው ሰላም ወዳድ ለሆነው ህዝብ ደግሞ የመሠረተ ልማት ችግሮቻችን ሊፈቱልን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል ።

የቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽ አለመሆን፣ የቦንጋ ብሔራዊ ቡና ሙዚየም ወደ ስራ አለመግባት፣በከተማው የስራ አጥ ቁጥር መጨመር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባውም ጠይቀዋል።

ከቦንጋአመያ፣ከዲሪማሻ እንዲሁም ከቦንጋ ስኳር ፋብሪካ ያሉ መንገዶች ዘላቂ እልባት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነዋሪዎቹ በአጽንኦት ጠይቀዋል።

በጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች በስፋት የሚስተዋሉ በመሆናቸው ሊቀረፉ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ዜጎች በነጻነት ተዘዋውረው እንዳይሰሩ የሚገታ ተግባር በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

በሹመት፣በቅጥርና መሰል ጉዳዮች አሁንም በዘመድ አዝማድ የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮች መኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶት ሊፈተሽ ይገባልም ብለዋል።

በዞኑ ያደሩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ታቅደው ሊተገበሩ ይገባልም ብለዋል።

የዜጎችን ስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በአካባቢው የኢንዱስትሪ ፓርክ መሠረተ ልማት ሊዘረጋ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ነዋሪዎቹ እነዚህንና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን በተነሱት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሽ ተሰጥቷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ህዝቡ ላነሷቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ከህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ገዢና እንደመንግስት ወስደን የምንሰራቸው ናቸው ብለዋል።

በክላስተር አደረጃጀት ምክንያት በዜጎች ላይ እንግልት እንዳይኖር በክልሉ ህዝቡ ባለበት አካባቢ ሆኖ አገልግሎቱን እንዲያገኙ የላይዘን ጽ/ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የቦንጋ ብሔራዊ ቡና ሙዚየም የሀገር ሀብት በመሆኑ ያለበት ችግር ተቀርፎ ለአገልግሎት እንዲበቃ የቦንጋ ዩኒቨርስቲ ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ህገመንግስቱን ከሚንዱ አስተሳሰቦች በመራቅ መርህን የተከተለ አሰራር መዘርጋት ይጠበቃልም ብለዋል።

በሀገሪቱ በፓይለት ደረጃ የተገነቡና ወደ ስራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች የሚፈለገውን ያህል ውጤት እያመጡ ባለመሆኑ ሌሎች አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት በመንግስት በኩል የተያዘ ዕቅድ እንደሌለ ተናግረዋል ።

የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ በሰጡት አስተያየት ጥያቄዎች ሲመለሱ አዳዲስ ጥያቄዎች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው ብለዋል።

ችግሮችን ሁሉ በአንድ ጊዜ መፍታት የማይቻል በመሆኑ ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል ።

ከለውጡ ማግስት በርካታ ጉዳዮች ምላሽ እያገኙ መምጣታቸውንና ወደ ፊትም የሚመለሱ ጉዳዮች በመመካከር እና በመነጋገር እልባት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

የሚያለዩንና የሚያናቁሩንን ነጠላ ትርክቶች በመተው የጋራ የሚያደርጉንና ገዢ የሆኑ ትርክቶችን በማጽናት ልንሰራ ይገባልም ብለዋል።

የተሳለጠ አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል በማለትም ተናግረዋል ።

ከህዝቡ የተነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች መሠረታዊ እውነታዎች በመሆናቸው ለችግሮቹ መፍትሔ በጋራ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

በዕለቱ የነበረው ህዝባዊ ውይይት በካፋ ንጉስ የምርቃት ስነስርዓት በማድረግ እና የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በመዘመር ተጠናቋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *