የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና የምክክር መድረክ ተካሄደ

Spread the love

የክልሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወራት ጠቅላላ ጉባዔና የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄደ።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ደስታ ጥላሁን ፓለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን ፓለቲካዊ፥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ በመሆን በህግ የበላይነት እና በዜጎች ደህንነት በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ልምድ ሊዳብር ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ተወካይ አቶ መስፍን ተስፋዬ ለሀገራችን ልማትና ዕድገት ሰላም ወሳኝ እንደመሆኑ መጠን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገራችን ብሎም ለአካባቢያችን ሰላምና ዕድገት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

አክለውም የክልሉ መንግስት የተጀመረውን የጋራ ምክር ቤቱን የመደገፍ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የክልሉ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወራት የአፈፃፀም ሪፓርት በምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱም በክልሉ መንግስት እና በዞኖች የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ ለቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በርካታ ተግባራት ማከናወኑ ተመላክቷል፤ በሪፓርቱም በክልሉ ፓለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ከቀድሞው የተሻለ መሆኑ ተገልጿ።

በተጨማሪም የፓለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ለጋራ ምክር ቤት አባላት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል። ቀደም ሲል የክልሉ ፓለቲካ ፓርቲዎችን የጋራ ምክር ቤት ካቋቋሙ 7 ፓርቲዎች በተጨማሪ 4 ፓርቲዎች በህጋዊ መንገድ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በአካባቢው እንደሚንቀሳቀሱ የተገለፀ ሲሆን እናት ፓርቲ እና መኢአድ ፓርቲ ለጉባዔው ቀርቦ የጋራ ምክር ቤቱ አባል እንዲሆኑ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በመጨረሻም የስራ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ ምርጫ ተካሂዶ 4 ወንድ እና 1 ሴት በድምሩ 5 አባላትን የያዘ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ በማካሄድ እና በጉባዔው ፊት ቃለ-መሃላ በመፈፀም ተጠናቋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ፥ የክልሉ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚዎች፥ የክልሉ መንግስት ተወካይ፥ በጥቅሉ 8 ሀገራዊ እና 3 ክልላዊ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በእንዳለማው ጌታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *