



በምዕራብ ኦሞ ዞን በሁሉም አከባቢዎች የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሰረቱ በመፍታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና በትምህርት ዘርፍ የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዞኑ ያለውን የትምህርት ጥራትና ተደራሽ ችግር ለመቅረፍ መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተከናወነ ሲሆን በጀሙ ከተማ አስተዳደር በLLRP ፕሮጀክትና በከተማው ማህበረሰብ ቀጥተኛ ተሳትፎ የተገነባ የጀሙ ሞዴል ቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህፃናት ትምህርታቸውን በአቅራቢያ እንዲያገኙ ምቹ እድል መፍጠሩ ተገልጿል፡፡
የጀሙ የከተማ አስተዳደር ትምህርት ዩኒት አስተባባሪ አቶ አሸናፊ አሊ፤ በከተማ አስተዳደሩ 9 የመንግሰት መለስተኛና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጀ እና 2 የግልና የመንግሥት ቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንና በዚህም ትምህርት ቤቶች 3ሺህ 452 ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ አንድ የጀሙ ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጀ ትምህርት ቤት ግንባታ በፕሮጀክት ድጋፍ እና በህብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ በመገንባት በተያዘው በጀት አመት የመማር ማስተመር ስራ እንዲሰጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በከተማው ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረው ከጀሙ ሞዴል ቅድመ አንደኛ ደረጀ ትምህርት ቤት በተጨማሪ አንድ የግል መዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤት መኖሩንና የተሻለ ትምህርት ለህፃናት እየሰጠ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሞዴል ቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለወደፊቱ በተማሪዎች ህይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት በመሆኑ ትምህርት ቤቶቹ በግብአት አቅርቦትም ሆነ በአደረጃጀት የተሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተወሰነ ደረጀ ያለውን የግብአት ውስንነት ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ለትምህርት ጥራትና ውጤት መሻሻል ትምህርት ቤቶቹ ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅሞ እንዲሰሩ የማመቻቸ ስራ በሰፊው እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የጀሙ ሞዴል ቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሀብታሙ ደስታ፤ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ጥራትና ውጤት መሻሻል ጉልህ ሚና ስላላቸው ትምህርት ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንና ትምህርት ቤቱ 217 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ህፃናትን በእውቀት፣ በስነምግባርና በክህሎት ብቁ ሆነው እንዲያድጉ በመስራት በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ሞዴል እንዲሆኑና የተሻለ ውጤት በየትኛውም እርከን እንዲያስመዘግቡ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
ትምህርት ቤቱ በተወሰነ ደረጀ የትምህርት ግብኣት መሟላቱን የገለፁት ርዕሰ መምህሩ በትምህርት ቤቱ አስፈላጊውን ግብአት በማሟላት እና ግቢውን ለህፃናት የበለጠ ምቹ ለማድረግ በቀጣይ ከትምህርት ማህበረሰብና ጋር በቅንጅት የሚሰራና ለዚህም የመንግሰት ክትልና ድጋፍ ሊጠንከር የሚገባ እንደሆኑም አመላክተዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
