ከተሞች ለነዋሪዎችና ለግብር ከፋዮች ምቹ የሚሆኑት ግብር በተገቢው ሲሰበሰብ ነው። ወ/ሮ ህይወት አሰግድ

Spread the love

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት በታክስ ህግ ተገዥነት ዙሪያ በሚዛን አማን ከተማ ከሚገኙ የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ እንደገለፁት አንድ ሃገር ነፃና ሉአላዊ ሆኖ የራሱን ጸጥታ ሲያስከብርና መንግስት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሊመልስ የሚችለው ግብር በተገቢው ሲሰበሰብና ሃብት ሲኖር ነው ብለዋል።

ከተሞች ለነዋሪዎችና ለግብር ከፋዮች ምቹ የሚሆኑት ግብር በተገቢው ሲሰበሰብ ነው ያሉት የቢሮ ሃላፊዋ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ግብርን በታማኝነት መክፈል ያስፈልጋል ብለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ ኢ/ር ሰለሞን ሌዊ በመድረኩ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ከተማችን ሚዛን አማንን ለኢንቨስትመንተ ምቹና ለቱሪዝም ተመራጭ ለማድረግ ግብርን በታማኝነት መክፈልና የተሰበሰበውን ግብር በአግባቡ ለልማት የሚያውል መንግስት መንግስት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሁሉም ግብር ከፋይ ነጋዴ የልማቱ አካል እንደመሆኑ በነፃነት የሚነግድበትና ሰርቶ ከሚያገኘው ተገቢውን የመንግስት ግብር የሚከፍልበትና የልማቱ አጋዥ የሚሆንበት ከተማ ለመፍጠር ሁሉም ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ሃላፊ ረ/ፕሮፌሰር ታገል ወንድሙ በበኩላቸው የመድረኩ ዓላማ ከደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች የሚሰበሰበዉ ገቢ ኢኮኖሚዉ ከሚያመነጨዉ ሀብት ተገቢ የሆነ ግብር ሰብስቦ ሚዛን አማን ከሌሎች ከተሞች ጋር በልማት እና መልካም አስተዳደር ተወዳዳሪ ለማድረግ ነዉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ የግብር ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ በሆኑት አቶ አየነው እሸቴ የውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል ሲል የዘገበው የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሚኒኬሽን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *