ከአቧራ ወደ አሻራ የተለወጠው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብት

Spread the love

የመደመር መንግሥት ለቱሪዝሙ ዘርፍ በሰጠው ሰፊ ትኩረት እና ክትትል ዘርፉ ከአቧራ ወደ አሻራ እየተቀየረ ይገኛል።

በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ የተገነቡት ፕሮጀክቶች ቱሪስቶችን በመሳብ ሰፊ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እየፈጠሩ ነው።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የሀገራችን የቱሪዝም እንቅስቃሴ አመርቂ እመርታ በማሳየቱ የቱሪስቶች ፍሰት እየጨመረ ነው ብለዋል።

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመፍጠር እና ነባር መዳረሻዎች እና ቅርሶች ላይ እሴት በመጨመር የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም አቅም እንደፈጠረም ይነገራል።

የቱሪዝምን አድማስ በማስፋት በዓይነት እና በጥራት በመጨመር እንደ ንግድ እና ሃይኪንግ መሰል አሠራሮች ስለመካተታቸው ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

መንገድ፣ መብራት እና ቴሌኮምን የመሳሰሉ የመሠረተ ልማት ግብዓቶች ለቱሪዝሙ ዕድገት አስተዋፅኦ አድርገዋል።

በያዝነው በጀት ዓመት የጀመሪያው ሩብ ዓመት 376 ሺህ 615 የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች የተለያዩ መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውን ዶክተር እንደገና ገልጸዋል።

ይህም ከባለፈው ዓመት ተሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ36 ሺህ 370 ቱሪስቶች ጭማሪ አሳይቷል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከሠራቸው የሪፎርም ሥራዎች መካከልም የመካከለኛው የምሥራቅ እና የባህረ ሰላጤ ሀገራት ቱሪስቶችን መሳብ ላይ ማተኮሩ እንደሆነ አንስተዋል።

በዚህም ከሳዑዲ ዓረቢያ እና ከአንዳንድ የባህረ ሰላጤ ሀገራት ከሐምሌ 2017 እስከ ኅዳር 2018 ድረስ በየወሩ ከ2 ሺህ 400 በላይ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንደጎበኙ ገልጸዋል።

በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለሸገር የተገነቡ የቱሪዝም መረዳሻዎች ቅንጡ እና ሳቢ በመሆናቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጎብኚዎች ተመራጭ እያደረጓቸው ነው።

የብሪክስ ሀገራት በቱሪዝሙ ዘርፍ እያሳዩት ባለው እመርታ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት እየተቸራቸው ነው ያሉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያም የብሪክስ አባል እንደመሆኗ ተጨማሪ እሴት እንደሆነላት እና የቱሪዝም የገበያ ድርሻ ከፍ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምታስተናግዳቸው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች የግል ተቋማት፣ በቱሪዝም ጉብኝት ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሰፊ ሥራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

#EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *