የሙስና ትግሉን በዘላቂነት ለማስቀጠል በአሰራር ብቻ የሚመራ ጠንካራ ተቋም መገንባት ይገባል፦ አቶ ንጉሴ ወ/ጊዮርጊስ

Spread the love

‎”ትውልድን በስነ-ምግባር፤ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ቃል 22ኛ ዓለምአቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ መርሐግብር በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

‎በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ወ/ጊዮርጊስ ሙስና ለሀገር ዕድገት ማነቆ በመሆኑ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል።

‎በክልሉ ህብረተሰቡ ባሳተፈ ትግል ሙስናን የመከላከል አቅም ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው በሙስናና ብልሹ አሰራር የተገኙ ሀብት የማስመሰል ስራም መሰራቱን ገልጸዋል።

‎ሙስናን በዘላቂነት ለመታገል በአሰራር ብቻ የሚመራ ጠንካራ ተቋም መገንባትና በስነምግባር የታነፀ ትውል መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራ መሆኑንም አቶ ንጉሴ ተናግረዋል።

‎የክልሉ ስነ-ምግባር ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙሉሸሰው ዘውዴ በበኩላቸው በክልሉ ሙስናን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

‎የሙስና መከላከል ስራ በአንድ ጀምበር የሚከናወን ባለመሆኑ ደካማና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ አሰራሮችን ማስወገድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

‎ሙስና ለሀገር እድገት እንቅፋት በመሆኑ በትውልድ ግንባታ ላይ በቁርጠኝነት በመስራት የሙስናን አስተሳሰብ ከስሩ ማጥፋት እንደሚገባም ተናግረዋል።

‎በዓሉ በድራማ፤ በጥያቄና መልስ ውድድርና ሙስናን መታገል በሚያስችሉ ኩነቶች እየተከበረ ይገኛል።

‎በማጠቃለያው መርሐግብር የክልል፤ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች፤ በዘርፉ የሚያገለግሉ መንግስት ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *