




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ለክልልና ዞን ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራርና አባላት የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የግንዛቤ መፍጠሪያ እና የጋራ የውል ስምምነት መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካኸደ ነው።
መድረኩ ዘመናዊ የህዝብ አስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችሉ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት በሚቀላጠፍበት ጉዳዮች ላይ ከመሪ ተዋንያኖች ጋር ለመግባባት እንደሆነ ተገልጿል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ልዩ አማካሪ አቶ ሰብስቤ ሻዎኖ መንግስት በመረጃ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት እና ውሳኔ ለዜጎች ለመስጠትና የፖሊሲ ግብዓት ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁሉም የሚታወቅባትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግና አንድ ሰው አንድ ብቻ መሆኑን ለማረጋገጥ የኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊ ስለሆነ የሐይማኖት ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ አሻራቸውን እንዲያኖሩም አሳስበዋል።
በክልላችን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ያወሱት ልዩ አማካሪው አልፎ አልፎ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የሐይማኖት አባቶች ምዕመናቸውን በማገናዘብ በቅርቡ የሚጀመረውን የቤተሰብ ምዝገባ እንዲያቀላጥፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሠለሞን ደነቀ ወሳኝ ከነቶች ምዝገባ ዜጎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በፍትሐዊና ቀልጣፋ መንገድ እንዲያገኙ ለማስቻል ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩን አዋጆች ያስቀሩን ቁልፍ ጉዳዮች በማካተት አዋጅ ቁጥር 1370/2017 ጸድቆ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት አቶ ሠለሞን በቅርቡ ለሚጀመረው ሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ የሐይማኖት ተቋማት አመራሮችና አባላት የኩነቶች ምዝገባን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ቃላችንን ሊናድስ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎችና የሐይማኖት ተቋማት አመራሮች የተገኙ ሲሆን: በሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ጽንሰ ሀሳብ ላይ ያተኮረ ሰነድ እየቀረበ ይገኛል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
