

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመገናኛ ብዙሃን ተቋም የሆነው የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ፣ የህዝብ ብሮድካስት የቴሌቪዥን ስርጭት አገልግሎት ለመስጠት ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ይፋዊ ፈቃድ ዛሬ አግኝቷል።
ይህ ፈቃድ የሚዲያ ተቋሙ የክልሉን ማህበረሰብ በተሟላ መረጃ ለማገልገል የጀመረውን ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ታሪካዊ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።
በዛሬው ዕለት በባለስልጣኑ ጽ/ቤት በተካሄደው የፈቃድ ርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የሚዲያ ኔትወርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ መኩሪያ እና ምክትላቸው ዶ/ር ካሳሁን ወዳጆ ፈቃዱን ከባለስልጣኑ ሃላፊዎች እጅ በይፋ ተረክበዋል።
የቴሌቪዥን ስርጭቱ መጀመር፣ ሚዲያ ኔትወርኩ “በመረጃ የበለጸገ ህብረተሰብ ተፈጥሮ ማየት” በሚል ራዕይ የጀመረውን ጥረት የሚያጠናክር ትልቅ ምዕራፍ ነው። ይህ ፈቃድ ተቋሙ በክልሉ ውስጥ ያለውን የመረጃ ተደራሽነት በማስፋት የህዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት የሚያስችለውን ቁልፍ እንደተረከበ ያሳያል።
የቴሌቪዥን ስርጭቱ መጀመር በክልሉ የሚገኙ በርካታ ዜጎችን በቀላሉ ለመድረስና የሚዲያ ተደራሽነትን ለማስፋት ወሳኝ ነው። ኔትወርኩ በዚህ ፈቃድ አማካኝነት የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቶችን ለህዝብ በማድረስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሚዲያዉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
