




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥብቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም በጀት ድጋፍ አሲዳማ አፈር በኖራ በማከም በስንዴ ምርት ላይ በኩታ ገጠም አመራረት ዘዴን ማስተዋወቅና የማስፋት የአርሶ አደር መስክ ጉብኝት ፕሮግራም ተካሄደ።
በሼይ ቤንች ወረዳ በመሃ ቀበሌ በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ ላይ አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም በስንዴ ምርት ላይ በኩታ ገጠም ማሻሻያ ቴክኖሎጂ የተሰራ 10 ሄክታር የስንዴ ማሳያ የመስክ የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ፤ ግብርና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ አንስተው በዘርፉ ሁለንታናዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሰሩ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎች አይነተኛ ማሣያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አራት አመታት በአፈር አሲዳማነት ላይ በተሰራው የቴክኖሎጂ ውጤት መሬትን በኖራ በማካም የግብርና ምርታማነት በአመት በአማካይ በሄክታር አንድ ኩንታል እየጨመረን መጥተናል ብለዋል፡፡
አቶ አሸናፊ አክለውም የአፈር አስዳማነት በተገቢው ማካም ከተቻለ የስንዴ ምርታማነት በሄክታር አሁን ከነበረው 35 ኩንታል ወደ 50 እና 60 ኩንታል ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ይህ በሼይ ቤንች መሃ ቀበሌ በኩታ ገጠም የለማ ማሣ ማሳያ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
አርሶአደሩ በቀጣይ የተሻለ ምርት ለማግኘት የግብርና ባለሙያዎች እና ዞኑ የሚሰጠውን ምክረ ሀሳብ መጠቀም እና ለሌሎች ተሞክሮአቸውን ማስፋት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የግብርና መሠረታዊ የሆኑ ችግሮችን በመለየት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ግብርናን ለማዘመንና ለማላቅ መሠረታዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወሳኝ በመሆኑ የክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ባሉት ሁለት የምርምር ማዕከላት የምርምር ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል የሚገኝ ብለዋል፡፡
በዚህም የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በአራቱ ዞኖች ላይ በርካታ የምርምር እና የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንና ከነዚህም ስራዎች አንዱ ለግብርና ስራ ማናቆ የሆኑ ችግሮችን መለየትና መፍትሔ የማዘጋጃ ተልዕኮ እየተወጣ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በክልሉ 864 ሺህ ሄክተር በአሲዳማነት የተጠቁ፣ ለምርታማነት ማናቆ የሆኑ እና የአርሶ አደሩን ምርት የሚቀንሱ መሬቶች መኖሩን የተናገሩት አቶ አማኑኤል በኖራ በማካም የምርታማነት መጠን በ20 ኩንታል እንዲያድግ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የግብርና ምርምር ሴክታር ግብርናውን ዘርፍ ለማሻገር የምርምር ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አንስተው በየደረጃው ያለው መዋቅር እና አርሶ አደር ማህበረሰብ የምርምር ቴክኖሎጂዎችን በተገቢው መጠቀም እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና አካባቢ ጥብቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ፤ በመሃ ቀበሌ በ10 ሄክታር 22 አርሶአደሮች በመሆን በኩታ ገጠም የዘሩት መስራች የስንዴ ዝሪያ መሆኑንና በቀጣይ ለዘር መጠቀም እንደሚቻል ገልጸው ይህንን በማስፋት አርሶአደሮችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በሰፊው እንደሚሰራም ተናግረዋል።
አርሶአደሮቹ አሲዳማ አፈርን በኖራ ለማከም 20 ኩንታል ኖራ በሄክታር የተጠቀሙበት እና በኩታ ገጠም መዝራታቸው የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ምርታማነቱ በማሳ ላይ ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የወረዳው ምክትል አስተዳደሪ አቶ ጎበዜ ስሳይ እንደገለፁት በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በአፈር ለምነትና ጤንነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በ10 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በኩታ ገጠም ማልማት መቻላቸውን ገልፀው ምርታማነቱ እጅግ የተሻ መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 40 ኩንታል ኖራና 25 ኩንታል ምርጥ ዘር በመጠቀም ከቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በቅንጅት የተሰራ መሆኑንና የወረዳው በFSRP/በስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም/ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልፀዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ ሞዴል አርሶ አደሮች፣ የወረዳ እና ቀበሌ አስተዳዳሪዎችና የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ አሲዳማ አፈር በኖራ በማካም በተሰራው የስንዴ ሰብል አመርቂ ልምድ ያገኙበት መሆኑ ተናግረዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
