



ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሳካት አጋዥ የቴክኖሎጂና የምርምር ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መሳካቱን መግለጻቸው ይታወቃል።
በተለይም በሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አንስተው፥ ኢትዮጵያ ወሳኝ በሚባል ደረጃ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት መሸጋገሯን ተናግረዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ም ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መሠረት በማድረግ መዘጋጀቱን ጠቅሰው ተደራሽነትን ማስፋት፤ እኩል እድልን በማመቻቸትና በተቋማትና ህዝብ መካከል መተማመንን የመፍጠር ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት አብራርተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እንዳሉት፥ ዲጂታላይዜሽንን በማፋጠን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግቦችን ለማሳካት በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ ምርምር ላይ አተኩረው እየሠሩ ነው።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር)፦ በዩኒቨርሲቲው ባለው የፈጠራ ማጎልበቻ ማዕከል የፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ፓተንት ያገኙ ፈጠራዎችን እያፈለቁ መሆኑን ጠቁመው ወደ ምርት የገቡ ስታርትአፖች መኖራቸውንም ነው ያስረዱት።
ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት የፈጠራ ሥራዎችን ማስፋፋት ወሳኝ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችና ባለድርሻ አካላት በትብብር በመሥራት የአቅም ግንባታ ሥራን ማጎልበት እንደሚገባቸው ነው የገለፁት።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለመሆን በያዘው ግብ መሠረት ለዲጂታል እውቀትና ቴክኖሎጂ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዲጂታላይዜሽንን ለማስፋፋት የመሠረተ ልማት ዝርጋታና አቅም ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና መምህራን በ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭና በሌሎች ማዕቀፎች የዲጂታል እውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ እንደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉ የትምህርት መርሃ ግብሮችን በመክፈት ተማሪዎችን በማብቃት ላይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ከኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታደሰ ረጋሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ዘመኑ በሁሉም ዘርፍ ቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽንን የሚጠይቅ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂ ማዕከል መሆን አለባቸው።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባሉበት አካባቢ የተፈጥሮ ፀጋን ተጠቅመው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዲጂታል ፈጠራ ሥራዎችን ማስፋት አለባቸው ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ከዚህ አኳያ ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በቡና ምርትና ሌሎች የአካባቢ ጸጋዎች ላይ የምርምርና የቴክኖሎጂ አገዝ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጠል ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
