




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እና ዕዳ አመላለስ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን የሚቀርፍ የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር (E-VOUCHER) ሥርዓት የግብርና ግብዓት ሽያጭ ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያ መረሐ- ግብር በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
የማስጀመሪያ መረሐ-ግብሩ የክልሉ ግብርና ቢሮ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በጋራ አዘጋጅነት ነው የተከናወነው።
በመረሐ-ግብሩ በክልሉ ቀደም ሲል በካፋና በቤንች ሸኮ ዞን በሦስት ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምረው ውጤታማ የሆነው የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር የዲጂታል ስስቴም በክልሉ በተቀሩት ወረዳዎች አሰራሩን ማስጀመር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ተደርጓል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ እውን ለማድረግ እንደክልል በልዩ ትኩረት ተግባራትን በማከናወን የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር ስስተም የአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ስርዓቱን በማቀላጠፍ የግብዓት ተጠቃሚ አርሶ አደሩን ቀጥታ ከሻጩ ጋር በማገናኘት የግብዓት ሽያጭ ገንዘብ በጊዜ ወደ የፋይናንስ ተቋም እንዲገባ የሚያስችልና ከገንዘብ ብክነትና ዕዳ ጫና የሚታደግ አሰራር እንደሆነም አንስተዋል አቶ ማስረሻ በላቸው።
በክልሉ የሚተገበረው የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር ዲጂታል አሰራር ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን የመረጃ አያያዝ፣ አስፈላጊ ግብዓት ማሟላት፣ አርሶ አደሩ ግብዓቱን በቅርበት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንዲሁም የግብዓት ሽያጭ ገንዘብ ቀጥታ ወደ ፋይናንስ ተቋም የሚገባበትን አሰራር ለመፍጠር በልዩ ትኩረት ሥራዎች ይከናወናል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማሜ ጋሩማ፤ በክልሉ ወደ ትግበራ የሚገባው የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር ዲጂታል አሰራር ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
የኤሌክትሮኒክ ቫውቸር ዲጂታል አሰራር ከዚህ ቀደም ከግብርና ግብዓት ሽያጭና ዕዳ አመላለስ ጋር በተያያዘ ይስተዋሉ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን በመቅረፍ አለአግባብ የሚባክነው ሀብትና የአርሶ አደሩን ጊዜ የሚቆጥብ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ሚናቸውን እንደሚወጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
በፍቅር ከበደ
