መንግስት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ የምግብ ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ ይገኛል – የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

Spread the love

መንግስት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎቻችንን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ የምግብ ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ ህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃቀዮችም የተሟላና ያልተቆራረጠ የምግብ ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ኮሚሽኑ ገልጿል።

ለተፈናቃዮች ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም የሚለው ዘገባ የተሳሳተ መሆኑንም ነው ያመለከተው።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ ህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ኮሚሽኑ መንግስት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎቻችንን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ የምግብ ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ እንደሚገኝ አመልክቷል።

ሆኖም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎቻችን የሰብአዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው የሚገልጽ የተሳሳተና የመጠለያ ጣቢያውን አጠቃላይ ሁኔታ የማይገልጽ ዘገባ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል።

የሰብአዊ ድጋፍን በሚመለከት በመደበኛነት አመቱን በሙሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የምግብ ስርጭት ሳይቆራረጥ እየተከናወነ እንደሚገኝ በመግለጫው አስታውቋል።

በህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያም የሚገኙ ዜጎቻችን ዓመቱን ሙሉ ተመሳሳይ ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበረ መሆኑንና ከመስከረም ወር 2018 ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር 2018 ድረስ የተሟላና ያልተቆራረጠ የምግብ ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።

በእስገደ ወረዳ ህፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ባለፉት አራት ወራት ለ14ሺህ 413 ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን አውስቷል።

በተጨማሪም ከአጎራባች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን ጨምሮ በመስከረም ወር 16ሺህ 775፣ በጥቅምት ወር 18ሺህ 290፣ በህዳር ወር 17ሺህ 813 እንዲሁም በታህሳስ ወር ለ14ሺህ 413 ዜጎች የሚያስፈልግ ምግብ መሰራጨቱን አመልክቷል።

በዚህም በድምሩ 11ሺህ 406 ኩንታል ምግብ (ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጥራጥሬና የምግብ ዘይት) ባለፉት አራት ወራት እንዲደርሳቸው መደረጉን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን ከ257 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑም ነው በመግለጫው ያስታወቀው።

በሌላ በኩል በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ የሰብአዊ ድጋፍ ችግሮች መኖራቸውንና ተጨማሪ የፌዴራል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጥያቄ ቢቀርብ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ መፈጸም የሚያስችል ዝግጁነት እንዳለም አመልክቷል።

ለተፈናቃይ ማህበረሰብ የሚላከው ድጋፍ ለታለመለት አላማ ብቻ መዋሉን የማረጋገጥና ክፍተቶች ቢኖሩም እንዲሟላ የማድረግ ኃላፊነት የክልሉና የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል።(ኢዜአ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *