


“ጎበዝ” የተሰኘ የቻይና አምራች ድርጅት የሶላር ምርቶችን ከዚህ ወር ጀምሮ ለውጪ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) አስታወቁ።
ኮሚሽነሩ ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 እንደተናገሩት ድርጅቱ በሶላር ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት በሶስተኛው “ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ ፎረም” ላይ ስምምነት የፈረመ ነው።
ድርጅቱ 250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈሰስ በማድረግ በስምንት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መግባቱንም ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው 3ኛው “ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ” ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ፎረም ላይ ከ1.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የፈረሙ አምስት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ስራ መጀመራቸውንም ኮሚሽነር ዘለቀ ጠቁመዋል።
በሶላር ዘርፍ ለመሰማራት ስምምነት የፈረሙት ኦሪጅን እና ሉምንቲክ ድርጅቶችም በጥር ወር ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚጀምሩ ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ቶዮ ሶላርን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በፎረሙ ከድርጅቱ ጋር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ስምምነት ማድረጉን አስታውሰዋል።
በቀጣዩ ፎረምም ከቃል አልፈው ወደ ተግባር የሚለወጡ ስምምነቶች እንዲኖሩ በአላማ ተኮር የማስተዋወቅ ዘዴ ከተለዩ ድርጅቶች ጋር ኮሚሽኑ እየተነጋገረ ነው ብለዋል።
ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 4ተኛው ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ፎረም የፊታችን መጋቢት ወር እንደሚካሄድ መዘገባችን አይዘነጋም ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
