





በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አደም መሃመድ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከመጅሊስ እስከ ካውንስል ድረስ ብቃት ያላቸውን መሪዎችን በመምረጥ ሙስሊሙ ሀይማኖታዊና ሀገራዊ ተልዕኳችን በአግባቡ መወጣት የጀመረበት ወቅት መሆኑን ገልፀዋል።
ወጣቱ ከተደራጀና ከተደገፈ ከሀይማኖት አልፈው ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን መወጣት የሚችል በመሆኑ ወጣቱን የሀገር አለኝታ አድርጎ መቅረፅ ያስፈልጋል ብለዋል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሰላም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ ታምሩ በበኩላቸው በክልሉ የሰላም እሴት ግንባታ ላይ የእስልምና እምነት አርዓያ መሆኑን ገልፀው አሁንም ለሰላም መስራታቸውን አጠናክሮ እንድያስቀጥሉ ጠይቀዋል።
ሁሉም ኃይማኖቶች ሰላምን፣ ተስፋን ፣መቻቻልን፣ ርህራሄና ፍቅርን ብቻ ማስተማር እንደሚገባቸው የእምነቱ አስተምሮ ቢገልፅም ከዚህ በተቃራኒ የማቆሙ በሚገጥሙበት ወቅት በጋራ ማውገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያን ባስጀመረችበት ማግስት የሚቋቋመው የሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ለሀገር ሰላምና ብልፅግና የራሱን ድርሻ ይወጣል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል።
የካፋ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ታከለ ታምሩ የግጭት መሰረቶች ፈርሰው የሰላም አምዶች እንዲጠናክሩ ከሙስሊም ወጣቶች ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዚዳንት ኡስታዝ ሀይደር ከድር ካውንስሉ ለትርፍ ያልተቋቋመ የሰላምና የዕድገት ወኪል የሆነውን ወጣት ለማፍራት ያለመ አደረጃጀት እንደሆነ ገልፀዋል።
ወጣቱ የሀገር ብልፅግና ሰላም ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፋተኛ በመሆኑ ሙስሊም ወጣት ይህንን ተገንዝቦ ሚናውን በአግባቡ ልወጣ ይገባል ብለዋል።
ካውንስሉ ኡስታዝ ሀይደር ሁሴን የክልሉ የሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዚዳንት እንድሁም ወጣት ከድረ አባገሮን የካውንስሉ ምክትል ፕሬዝዳንትና ሌሎች አስራ ሁለት አባላት ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
በንጉሰ ወልደየስ
