በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ የቀሩ ህጻናት የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው – ደስታ ገነሜ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ የቀሩ ህጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ “የተፋጠነ ትምህርት መርሐ ግብር” ስልጠና በቦንጋ እና በታርጫ ከተሞች እየሰጠ ይገኛል።

በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የትምህርት ዕድል ያላገኙ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባትና የትምህርት ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትልና የመማር ማስተማር ዘርፍ ሀላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር) የገለጹት።

የተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም ከ9 ዓመት እስከ 14 ዓመት በእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና በተለያዩ ችግሮች ትምህርት ቤት ያልገቡ ህፃናትን በ18 ወራት ውስጥ ከ1ኛ ክፍል-3ተኛ ያለውን የትምህርት ክፍል በማጠናቀቅ በቀጣይ ዓመት 4ተኛ ክፍል ከዕድሜ እኩያቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ የሚያስችል መርሐ ግብር መኾኑን ነው ዶ/ር ደስታ የገለጹት።

ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉ መምህራን በቀጣይ በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ የራቁ ህፃናትን ከእድሜ እኩያቸው እንዲደርሱ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ዶ/ር ደስታ አስገንዝበዋል።

ፕሮግራሙ ራሱን የቻለ ስርዓተ ትምህርት ያለው ነው ያሉት ዶ/ር ደስታ ከ1ኛ እስከ 3ተኛ ክፍል ያሉ የስርዓተ ትምህርት ሂደቶችን ያካተተና ተማሪዎቹ በመሰረታዊነት አጥጋቢ የሆነ በመማር ክህሎቶችን መሠረት አድርገው የሚማሩበት መሆኑን አስረድተዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራር ተግባሩ እንዲሳካ በቁርጠኝነት መደገፍ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ዶ/ር ደስታ፥ ሰልጠኞች በስጠናው ያገኙትን እውቀት ከተግባር ጋር በማቀናጀት የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።

ስልጠናው በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች ለተወጣጡ 106 መምህራን በቦንጋ እና በታርጫ ከተሞች እየተሰጠ እንደሚገኝም ዶ/ር ደስታ ጨምሮ ገልጸዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *