የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

Spread the love

ባለፉት ተከታታይ ወራት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ አጠቃላይ የክልሉን ገጽታ የሚያሳዩ እና የስድስቱ ዞኖች የተለያዩ ባህላዊ ይዘቶችን የዳሰሱ ጽሁፎችን እንደየቅደም ተከተላቸው ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬ በዚሁ አምድ”በቤንች ሸኮ ዞን “የቤንች ብሔረሰብ ባህላዊ ዳኝነትን” ሊናስቃኛችሁ እንወዳለን።

መልካም ንባብ!

የቤንች ብሔረሰብ ለዘመናት ያቆያቸው የራሱ ቋንቋ ፣ባህል ፣ታሪክ ቅርስ ትውፊት ያለው ነው፡፡ ከእነዚህ የባህል እሴቶች መካከል አንዱ የግጭት አፈታት ስርዓት የሆነው ባህላዊ ዳኝነት  ነው፡፡

ብሔረሰቡ እንደዛሬው ዘመናዊ ዳኝነት ባልነበረበት ጊዜ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ኤርግ፣ (ድዴ ኤርግ) ተብሎ የሚጠራ የባህላዊ ዲኝነት ስርዓት አላቸው፡፡

በዚህ የእርቅ ስርዓት በብሔረሰቡ አባላት መካከልና ከሌሎች ጋር የሚከሰቱ ያለመግባባቶችና ግጭቶች ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሳቸው አስቀድሞ እልባት በመስጠት ዜጎች በፍቅርና በሠላም የአመለካከትና የተግባር ልዩነቶች ሳይበግራቸው ተቻችለው እንዲኖሩ በማድረግ ላይ ያለ እሴት ነው፡፡

የባህላዊ ዳኝነት እና የእርቅ ሥነ-ስርዓት ወይም ሽምግልና በተጋጩ ወገኖች መካከል የተከሰተውን ያለመግባባቶችን ወደ እርቅ ለማምጣት በአስታራቂ አባቶች (ሽማግሌዎች) አማካኝነት ይፈጸማል፡፡
የባህል ዳኞቹ ወይም ሽማግሌዎቹ በማህበረሰቡ ዘንድ የተከበሩ፣ የተመሰገኑና በስነ- ምግባራቸው የተመሰከረላቸው የዕዴሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡

ዳኝነቱና የእርቅ ስነ-ስርዓት ዘርፈ ብዙ ፋይዲዎች ያለው ሲሆን በዋናነትም ያለመግባባትን በሀይል እርምጃ ከማስወገድ ይልቅ በዳይና ተበዳይን አገናኝቶ በመዳኘት አግባብቶ የተፈጠረውን ቅራኔ በቶሎ በመፍታት የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ወደ ሠላምና መረጋጋት ይቀይራል፡፡

በተለያዩ ጥቃቅን ምክንያቶች የተጋጩ ወገኖችን የጋራ ተጠቃሚ በማድረግ ከይቅር ባይነት ፍቅር ያስተሳስራል፤ የግጭቱ ተሳታፊዎችም ሆነ ገለልተኛ ወገኖች ያለስጋት በሠላም ወጥተው በሠላም እንዲገቡና ተበዳይ ወገን ለብቀላ ራሱን እንዳያዘጋጅ በእቅጩ ቋጭተው አብሮ እንዲኖሩ ያግዛል፡፡

ባህላዊ ዳኝነቱና የእርቅ ስርዓቱ ከአድሎአዊ አሰራር፣ ከሙስናና ተያያዥ ግላዊ ጥቅም የጸዳ ሆኖ ይመራል፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ውሸት፣ ማጭበርበር፣ ጥላቻ፣ ክህደት፣ ስርቆት፣ እምነት ማጉደል የመሳሰሉ ተቃራኒና አፀያፊ ተግባራት እንዳይኖር ላቅ ያለ አበርክቶ ያደርጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዘመናዊ ዳኝነት ሂደት የሚወጡ ወጪዎችንና የሚባክነውን ውድ የስራ ጊዜ ከመቆጠብ አልፎ የፍትህና የፀጥታ ስራ ጫናዎችን ይቀንሳል፡፡

የዳኝነቱ ሂደት በአብዛኛው የተበዩዩን በደል መርምሮ ሁለቱን አካላት በማሳመን ተበዳይን መካስና በመጨረሻ ማስታረቅና እርቀ-ሠላም በማውረድ ወደ ቀድሞ መልካም ግንኙነታቸውና አብሮነት መመለስ ነው፡፡

በብሔረሰቡ አባላትና በአጎራባች ብሔረሰቦች መካከል አንዳንድ አለመግባባቶች ተከስተው ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት የሚፈታበት ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ከመንደር ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የንጉሱ ስርዓት የተዘረጋ የራሱ የሆነ የስልጣን መዋቅር (ደረጃ) የተደራጀ ነው፡፡

ቲያት (ንጉስ)፣ ጠቅላይ፣ ገዢ፣ ጊያስ፣ ባብ (ፈራስ) ገበራስ (ጠመራሻ) የመጨረሻው ህዝብ ሲሆን ማንኛውም የፍርድና የአስተዲደራዊ ጉዳይ የአሠራር ስርዓት ሰንሰለቱን ጠብቆ ተግባራቱን ይፈጽማል፡፡

ዳኝነቱ የሚሰጥባቸው ጉዲዮች በግድያ ፣በድንበር፣ በግጦሽ መሬት፣ በጠለፋ፣ ጋብቻ እና የእምነት ክህደት በመሳሰሉት የሚነሱ ግጭቶችን እንደየጉዳዩ ክብደት ዳኝነቱ በቶምቴት የሚታይና የሚዲኝ ሲሆን ጉዲዮቹ ምስክርና ማስረጃ የሌላቸው፣  በፍርድ ቤቶች ወይም በዘመናዊ የዳኝነት ስርዓት መቋጫ ያጡ በዚህ ባህላዊ ዲኝነትና እርቅ ስነ-ስርዓት ችሎት ላይ ፍትህ ያገኛሉ፤ በአሁኑ ወቅትም በአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው፡፡

በብሔረሰቡ ዘንድ ግዴያ ሲፈፀም የወንጀል አፈፃፀም ከተጣራ በኋላ በሁለቱ ደመኞች የጋራ ድንበር ላይ ሠንጋ ታርዶ ራሱን የቻለ ዝርዝር ባህላዊ ስርዓት በባህላዊ እምነቱ መሰረት ተፈጽሞ በደም ይታረቃሉ፤ የእርቁ ስርዓት ማስፈጸሚያ ወልዳ የጨረሰች ላም (ከርሽን) ትሆናለች ፡፡

የገዳዩና ሟች ቤተሰብ በሙሉ ተሰብስቦ በየወገናቸው ሆኖ ተቀምጦ የግዲያው መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር አድርገው ከየጎሳው የተሰበሰበና ትክክለኛ ፍትህና ዳኝነት ይሰጣል፡፡

ዝርዝር አፈጻጸም በመሪው በተሾሙ እጅግ ታማኝና ልማድ ያላቸው ሽማግሌዎች ቁጥራቸው ከ4-6 ምዴብ ሆኖ ከሁለቱም ወገኖች በተሰየሙ አስታራቂ ፊት ዝርዝር አፈፃጸሙ ባህላዊ እምነትን መሰረት ተገልፆ የሟች ቤተሰብ እርቁን እንዲቀበል ተደርጎ የእርቁ ማረጋገጫ ሆና የቀረበችው ላም በቅድሚያ በገዳይና ሟች ቤተሰብ መካከል ቀርባ ገዳይ ተንበርክኮ ይቅርታ እንዲጠይቅ የሟች ቤተሰብም ይቅር ይለዋል፡፡

በሟችና ገዳይ ቤተሰብ መካከል ምንም ዓይነት ቂም በቀል፣ በጠላትነት መፈላለግ እንዲይፈጠር ጥብቅ ቃለ መሃላ ይፈፀማል፡፡ ቃለ መሀላውን ተላልፎ (ጥሶ) የተገኘ ከብሔረሰቡ ይገለላል፤ ይረገማል፣ የእርግማኑ አይነትና ዝርዝር በሽማግሌዎቹ ተራ በተራ ተደርድሮ የሟች ቤተሰብ ተንበርክኮ አሜን እያለ ህዝቡም ያስተጋባል፡፡

የእርቃቸው፣ የስምምነታቸውና መሀላቸው ምልክት ይሆን ዘንድ የገዳይና የሟች ቤተሰብ በወንዝ ማዶ ሆኖ የጠቡ መነሻ ሀጥያት ርኩሰት ያለመግባባት ደም መፋሰስ በዚህ ወንዝ ታጥቦ ይሂድ፤ ቂመኝነት፣ ጥላቻ፣ መገዳደል፣ በቀል ከልባችን ታጥቦ ይወገድ በማለት ሽማግሌዎች ይመርቃሉ፡፡

ቀደም ሲል ከአጥፊው በካሳ የተገኘችው ላም በአማቻቸው በኩል ትታረድና የላሚቱ አንጀት እንዲይበጠስ በጥንቃቄ እየተሳበ ከወንዝ ማዶ ባለው ወገን አማካኝነት ወንዝ ተሻግሮ በገዳይና ሟች ወገን አንዱን ይዘው አለመግባባት ግድያና መፈላለግ ከዚህ ዕለት ጀምሮ ከሁለቱም  ወገን ተወግዷል ተባብለው ወዲያውኑ በፍቅር ይቀላቀላል፡፡

በ አሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *