









የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሀ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ፤ በውሃና መስኖ፣ቆላማ አከባቢ እእንዲሁም የአከባቢ ጥበቃ ዘርፍ በክልሉ የተሰሩ እና እየተሰሩ ባሉት ዝርዝር ተግባራት ላይ ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በዚህም፥ ባለፉት አራት ዓመታት የክልሉ ምሥረታ አነስተኛ የነበረውን የውሃ ሽፋን ማሳደግ መቻሉ ተገልጿል።
ምንም እንኳን በክልሉ ከፍተኛ የከርሰምድርና ገጸ ምድር የውሃ ሽፋን እንዲሁም በመስኖ መልማት የሚችል ሰፊ መሬት ቢኖርም ከመሠረተ ልማት አኳያ ሰፊ ክፍተት ያለ በመኾኑ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት ተነስቷል።
በዘርፉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ኾኖ ስነሳ የቆየውን የቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ እና የሻርማ መስኖ ፕሮጀክት ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሻ መኾኑ ተጠቅሷል።
በአከባቢ ጥበቃ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወነ መኾኑ የተገለፀ ሲሆን በክልሉ ማኅበረሰቡን ከተፈጥሮ ሀብት ቀጥተኛ ተጠቃሚ በማድረግ የአከባቢ ጥበቃ ተግባር ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚሻ ተገልጿል።
በክልሉ ከፍተኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ኾኖ ስነሳ የቆየውን የቦንጋ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለጥናትና ዲዛይን ሥራ ማከናወኑ የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ ፕሮጀክቱ በሀገር ደረጃ በልዩ ዕቅድ ከተጀመሩ ተነጥሎ የቀረ በመኾኑ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።
ከ15ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ሰፊ የአርብቶአደሮች ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል ተብሎ የተጀመረው የሻርማ መስኖ ፕሮጀክት የክልሉ መንግሥት በከፍተኛ ሀብት ለጥናትና ዲዛይን ስራው መድቦ ስራው ቢጠናቀቅም በፕሮጀክት ፋይናንስ ምክንያት ወደ ተግባር ያለመግባቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እየፈጠረ መኾኑም በመድረኩ ተነስቷል።
በቆላማ አከባቢዎች ፍትሀዊ የልማት ተደራሽነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በአርብቶአደር አከባቢ የተጀመሩ የታዳሽ ሀይል አማራጭ በተገቢው ተከታትለው ወደ አግልግሎት ከማስገባት አኳያም ክፍተት መኖሩን ጠቅሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክብርት ፈትሀ አሕመድ በበኩላቸው በክልሉ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ የመስክ ምልከታ በማድረግ ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
