



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ከኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በካዳስተር ቅየሳ ዙሪያ ለዘርፉ ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠናው የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊና የከተማ መሬት መረጃና ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሔም ተሾመ በክልሉ በሁለተኛ ደረጃ እና ሶሰተኛ ደረጃ የመሬት መቆጣጠሪያ ነጥቦች ላይ ንባብ ለመውሰድና የመሬት መረጃ አያያዝ ወይም ካዳስተር ስራን ለማዘመን ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና ስልጠናው ስራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በክልሉ የዘርፉን ስራ በተፈለገው ልክ ለማስኬድ የመሣሪያ እጥረት ያለ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሬት ቅየሳ መሣሪያ/South DGPS/ በድጋፍ መልክ ማበርከቱን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
እንደ ወ/ሮ ቤተልሔም ገለጻ መሣሪያው እንደሀገር አዲስ ከመሆኑ የተነሳ በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ የክህሎት ክፍተት በመኖሩ የነበረውን ከፍተት ለመሙላት የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተወስዷል ብለዋል።
በስልጠናው ከሁሉም ዞኖች የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው ከንድፈ ሀሳብ ባሻገር ተግባር ተኮር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ተገልጿል።
በፍቅር ከበደ
