
ካደጉት ሀገራት የሚለቀቁ በካይ ጋዞች አማካኝነት በሚከሰት አየር ንብረት ለውጥ መዛባት ምድራችን ሲትናጥ: በታዳጊ ሀገራት ደግሞ በአካባቢ አያያዝና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ክፍተቶች ትፈተናለች።
እንደ ሀገር ይኸንኑ ችግር መቋቋም በሚያስችል መልኩ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አረንጓዴ አሻራ እና ጽዱ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ንቅናቄዎች ተግባራዊ ሆነው ውጤትም እየተመዘገበ ይገኛል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የክልሉን ተጨባጭ አሰተዋጽኦ በሚመለከትና የሚንታወቅበትን የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ልምድ ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚ ዕድገት መቀየር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አስራት ገ/ማሪያም (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!
መ/ኮ: በቅድሚያ ከዝግጅታችን ክፍል ጋር ቆይታ ለማድረግ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ!
ኢንጂነር አስራት (ዶ/ር): እኔም አመሰግናለሁ!
መ/ኮ: እንደ ክልል የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባትና የተቋማችሁን ግብ ለመምታት ምን እየተሰራ ነው?
ኢንጂነር አስራት (ዶ/ር): ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች የተስማማችባቸውን ውሎች ወደ ክልላችን አውድ በማምጣት ቀደም ብለው በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገውን አካባቢ መጠበቅ የሚያስችሉትን ስራ በደን ልማት፣ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ፣ በአካባቢ ጥበቃና ማህበረሰብ ተጽዕኖ ዘርፎች እያሳለጥን ነው።
በተፈጥሮ ሀብት (በደኑ) ዘርፍ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና በማስተባበር በክልሉ ምስረታ ጊዜ 41 በመቶ የነበረውን የደን ሽፋን ወደ 44 በመቶ ማሳደግ ተችለዋል።
የክልሉ ማህበረሰብ የሚታወቅበትን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ከአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ጋር በማቀናጀት በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ቦታዎች መልሶ የማልማትና የነበሩትን የመከለል ስራ ውጤት እያመጣ ነው።
ለቱሪዝምና እርሻ ኢንቨስትመንቶች ምቹ የሆኑ ስነ ምህዳራችን ተጠበቆ ኢኮኖሚ ማመንጨት እንዲችል ተቋማችን ይተጋል፤ ይሁን እንጂ የመንግስትን የበጀት ተደራሽነት ክፍተቶች የሚሞሉ ፕሮጀክቶች ዘርፈ ብዙ እምርታዎችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
ለአብነትም REDD+ በክልሉ ውስጥ 37 ወረዳዎችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ አሳታፊ ደን አስተዳደር ስራ እየሰራ ሲሆን ለዘላቂና ተሸጋጋሪ ተግባራትን የሚያግዙ 40 የችግኝ ጣቢያዎች ተዘጋጅተው ለእያንዳንዳቸው ከ 700 ሺህ በላይ ድጋፍ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ ገብቷል።
መ/ኮ: በፕሮጀክቶች ይፋ የሚሆኑ ድጋፎች ለታለመለት ስራ ስለመዋላቸው ማሳያዎች ይኖሩ እንደሆኑ ቢጠቅሱ
ኢንጂነር አስራ(ዶ/ር): ከዚህ ጋር በተያያዘ በደን ዙሪያ ላይ ኑሯቸውን መሠረት ላደረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ተደርገው ከሰልና የማገዶ እንጨት በማቅረብ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ከቀድሞ CRFL ጋር ተቀናጅተው እስከ ግማሽ ዓመት ድረስ 57 ሚልየን ብር ድጋፍ በተለያዩ እርባታዎችና ሆርቲካልቸር ሰብሎች እንዲሰማሩ ተደርገዋል፤ ውጤታማ እየሆኑም ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በክልላችን 6 ቡና አብቃይ ወረዳዎች ውስጥ በ30 ቀበሌያት ላይ ተግባሯዊ የሆነው FLOUR ፕሮጀክት በርካታ የግንዛቤና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
ይህ ፕሮጀክት ለእያንዳንዱ ወረዳ ከ 11 ሚልዮን ብር በላይ ድጋፍ: ሞተር ሳይክልና የቢሮ ቁሳቁሶች፣ ለቡና ጉንደላ የሚጠቅሙ 72 ማሽኖችን እንዲሁም የቡና ጉድጓድ መቆፈሪያ ቴክኖሎጂ በማምጣት በቡና ዕድሳት ላይ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ አሳድጓል።
ክልላችን ከቡና መገኛነት ባሻገር ምርታማነቱ ተሻሽለው በኢኮኖሚ ላይ የሚጠበቀውን ድርሻ እንዲወጣ ከ 700
ሄክታር በላይ ቡና ከማሳደሱም በላይ አርሶ አደሩ ለሚያድሰው ቡና ማሳ ድጎማ በማድረግ ሌሎችም ወደ ጉንደላ እንዲገቡ መነሳሳት እየፈጠረ ነው።
ፕሮጀክቱ ከዚሁ ስራ በተጨማሪ በማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎና ሶላሮች ድጋፍ ያቀረበ ሲሆን በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራም 7800 ሄክታር ክለላ ስራ ሰርቷል።
ከደኑ ጋር የተያያዘው የብዝኃ ህይወት ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ(በደን ውስጥና ከደን ውጭ ያሉ ብዝኃ ህይወት) ሀብታችን ተጠብቀው የሚቆይበት፣ የሚለማበትና ጥቅም በሚሰጡበት ጉዳይ ላይ ከአጋር አካላት ጋር እየተሰራ ነው።
መ/ኮ: በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የተሰሩ ስራዎችና የመጡ ለውጦች ካሉ ቢጠቅሱልን
ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): በፓርቲያችን መርህ ለህበረሰቡ ምቹ እና ንፅህ ከባቢ አየር ላይ የመኖር መብቱን ለማስጠበቅ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀናጅተን እየሰራን: ርዕሰ መስተዳደራችን እና የፌዴራል ስራ ኃላፊዎች በተገኙበት “ጽዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ ጀምሮ ተግባራትን እያከናወንን ነው።
ይኸንን ተግባራት የሚያግዝ በጀት መድበን በየከተሞች በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ አድርገን እየደገፍን ሲሆን በማይታረሙት መዋቅሮችና ተቋማት ላይ በከተማ ልማት ቢሮ በኩል በወጣው ደንብ መሠረት የአካባቢያቸውን ጽዳት 20 በ 50 ራዲየስ በማይጠብቁት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።
የቆሻሻ አያያዝና አስተዳደር ስርዓት እንዲዘምን ከNABU ኢትዮጵያ ጋር በመሆን ቦንጋ ከተማ ላይ ከየመንደሩ የሚወጣ ቆሻሻ የሚለይበት ሼዶች ተሰርተው ለመልሶ አገልግሎት(በስባሹ ለማዳበሪያ፣ ፕላስቲክ ከረጢቶች ለፋብሪካ ግብዓት) እንዲውል ተደርጓል።
ይህ ስራም ወደ ሌሎች ከተሞች እንዲስፋፋ ከከተማ መዋቅር ስራ ኃላፊዎችና ድርጅቶች ጋር በ700 ሺህ ብር የሚገዛውን መፍጫ ማሽን በመግዛት መሰል የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንዲዘረጉ መግባባት ላይ ደርሰናል።
መ/ኮ: ከፋብሪካዎችና ኢንቨስተመንቶች የሚወጡ በካይ ጋዞችን ለመከላከል ምን እየተሰራ ነው?
ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ በካይ ኬሚካሎች በማህበረሰቡ ላይ አደጋ እንዳያስከትሉ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ሲሆን ቀድመን አወንታዊ ተፅዕኖ ላይ በመስራት ከቡና ገለባዎች ከሰል የሚያመርት ማሽን በRED+ ድጋፍ ተገዝተው በተደራጁ ማህበራት በኩል ወደ ስራ እየገባ ነው።
በዚህ ተህባር ወጣቶች ተደራጅተው ከየ እንዱስሪዎች የቡና ገለባን ወደ ማሽኑ የማምጣት ስራ ላይ የሚሰማሩ ሲሆን በከሰል ፍላጎት የሚጨፈጨውን ደን በማትረፍ ረገድ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል።
ከዚህ ውጭ ከእሼት ቡና ማጠቢያ እንዱስትሪዎች፣ ከወርቅና ከሰል ድንጋይ ማምረቻዎች የሚወጡ በካይ ጋዞች ማህበረሰቡ የሚጠቀምባቸው ወሃ አካል እንዳይቀላቀል ክትትል እየተደረገ ሲሆን በ6 ወራት መታረም ባልቻሉት 26 ድርጅቶች ላይ ማስጠንቀቂያ ተሰጥው 2 ላይ ከፍተኛ እርምጃ ተወስደዋል።
ከቁጥጥር ስራ ቀደም ብለን የክልሉን ኢንቨስትመንት ፍላጎትና የአካባቢ ጥበቃ ስራ ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲኸዱ “በአካባቢና ማህበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ” እስታንዳርድ መሠረት ወደ ክልሉ የሚመጡ ኢንቨስትመንት ዕቅዶች ምርመራ ከማድረግ ጀምሮ አፈጻጸማቸውን እንንከታተላለን።
መ/ኮ: እንደ ክልል ሆነ እንደ ማህበረሰብ ይህ የደን ሀብታችን(44%) የኢኮኖሚ ድርሻ እንዲኖረው ምን እየተሰራ ነው?
ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): በክልላችን ማህበረብ ከደን ሀብቱ ጋር ካለው ቁርኝት በተጨማሪ የተጎዱትን እንዲያገግሙ የሚናደርግበት ትልቁ ግባችን ኢኮኖሚው ላይ ተገቢ ድርሻ እንዲኖረው ነው።
ይኸንኑ እውን ለማድረግ ከወንዶ ገነት ህጽዋት ማዕከልና ከኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወትና ጂኦ-እስፓሻል እንስቲትዩት ጋር በመሆን በተደራጀ ጥናት አስደግፈን የጀመርነው ሂደት እየተፋጠነ ነው፤ በቀጣይም ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ቀርበው ወደ የሚገባን ክፊያና ሞዳሊቲ ይሸጋገራል ብለን እናስባለን፤ ነገር ግን በአንድ ጀምበር የሚያልቅ ጉዳይ ነው ብለን አንጠብቅም።
በክልሉ ተመዝግበው ካሉት ሁለት ባዮስፌር ሪዘርቮች የካፋ ባዮስፌር ምዝገባ እንዲታደስ የተደረገ ሲሆን የሸካ ባዮስፌር ምዝገባ ሂደት ላይ ነው፤ ሌላ አንድ ተጨማሪ ተፈጥሮ ሀብት(የቤንች ሸኮ) UNESCO ላይ እንዲመዘገብም ሂደቶችን ጀምረናል።
መ/ኮ: ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋችሁ ጉዳይ ካለ ቢያስታውቁን?
ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የሁሉንም ተቋማትና ግለሰቦች አበርክቶ የሚጠይቀው ስራ ቢሆንም የክልሉ መንግስት በአካባቢያችን ላይ ያሉ ኢንቨስትመንቶች የመያመርቱት ምርት በተፈጥሮ ስነ ምህዳር ላይ ስለሆነ የከባቢ አየር ክፊያ (Payment for Ecosystem) ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት ማድረግ አለበት።
ከዚህ በተጨማሪ በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል 44% ደን ሽፋን የእርሻና ኢንቨስትመንት መሬት ቢሆን ሊገኝ የሚችለውን የኢኮኖሚ ድርሻ ከግምት በማስገባት የበጀት ቀመር አካል እንዲያደርግ ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።
መ/ኮ: ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ
ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ሚዛን መጠበቅ ጥቅሙ ለሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ስለሆነ ሁሉም ዜጋ የአካባቢውን 20 ሜትር ራዲየስ፣ ተቋማት 50 ሜትር ራዲየስ እያጸዳ ምቹ ከባቢ በመፍጠር ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲፈጥር እላለሁ።
በሌላ በኩል በደን አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍላችን እንደ ወትሮ ደኑን በመጠበቅና በመንከባከብ ለሚናልመው ካርበን ክፊያ ስርዓት እንዲያመሩ፤ ከሚያመነጨው ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማሳሰብ እወዳለሁ።
መ/ኮ: በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ ሰጥተው አስፈላጊውን ማብራሪያ ስለሰጡ በዝግጅታችን ክፍል አመሰግናለሁ!
ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): እኔም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታችሁ ስላቀረባችሁኝ አመሰግናሁ!
በአሻግሬ ገ/ወልድ
