በክልሉ ዘላቂ የጤና፣ ምግብና የትምህርት ልማት ሥራዎችን ለማሳካት ያላቸውን ቁርጠኝነት የተባበሩት መንግስታት የዓለም ዓቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች ገለጹ

Spread the love

የተለያዩ የተባበሩት መንግስታት የዓለም ዓቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የቀጣይ ድጋፍ አቅጣጫ ለመለየት ያለመ የልማት ሥራዎች ጉብኝት እና ከክልሉ መንግስት ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነዉ።

የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ፍራንሲስ ቺሳካ፤ በክልሉ በነበራቸው ቆይታ በክልሉ ያለውን እምቅ አቅም መመልከታቸውን ገልጸዉ በተለይም በትምህርት ቤቶች የተመለከቱት የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር ተስፋ ሰጪ እንደሆናቸውም አስረድተዋል።

በክልሉ በጤናዉ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን የተባበሩት መንግስታት የልማት አጋር ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ሲደግፉት ከነበረው በበለጠ እንዲደግፉ እንደሚሰራ የጠቀሱት ዶክተሩ፤ በተለይም በወባ በሽታ መከላከል የሚሰሩ ሥራዎችን ለማገዝ ተቋማቸው እቅድ መያዙንም አስታውቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥር የሚሰሩ ሁሉም አጋር የልማት ድርጅቶች ሥራቸውን በመናበብ ማከናወን ከቻሉ የሀገሪቱን እና የክልሉን ሁሉዓቀፍ ሥራዎችን ማሳካት ይቻላልም ብለዋል።

በክልሉ የአርሶ አደሮች ገቢና የእርሻ ዘርፉን ለማጠናከር የሚሰሩ ሥራዎች የበለጠ መጠናከር የሚገቡ ናቸው ያሉት ደግሞ የዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ኦርላንዶ ሶሳ ናቸዉ።

በተለይም በዓሳና ሩዝ ምርት በክልሉ የሚሰሩ ሥራዎችን ተቋማቸው እንደሚደግፉና በአከባቢው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርና ተቋማዊ ውይይት በማድረግ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩም አስረድተዋል።

ተቋማቸው በምግብ ዋስትና መረጋገጥና በትምህርት ቤት ምግባ ላይ እየሰራ ይገኛል ያሉት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የኢትዮጵያ ተወካይ ወ/ሮ ሙትንታ ሃምባይ፤ ተቋማቸው ትምህርት ቤቶችን በበጀትና በስልጠና በመደገፍ ለውጥ እንዲመጣ እያገዘ መሆኑን ገልጸው በቀጣይነት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ዓቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች በክልሉ ዘላቂ የጤና፣ ምግብና የትምህርት ልማት ሥራዎችን ለማሳካት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዉ ተቋሞቻቸው በተለያዩ ሀገራት ያከናወኑትን ምርጥ ተሞክሮ በኢትዮጵያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለማስፋፋት በትብብር እንደሚሰሩ አሳውቀዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *