






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግና ተቋማዊ አሠራርን ለማዘመን የጀመራቸው ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት የማኅበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።
ኮሚቴው የቢሮውን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው፤ ተቋሙ የመረጃ አቅርቦትን ጥራት ለማረጋገጥና የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለማስፋት የሄደበት ርቀት አበረታች ነው። በግምገማ መድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሐይ ዳርጫ፣ ቢሮው ሳቢና ወቅታዊ ይዘቶችን በማዘጋጀት መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
ተቋሙ ከክልሉ የሚዲያ ተቋማት ጋር የፈጠረው ጠንካራ ቅንጅት መረጃዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ለሕዝብ እንዲደርሱ ከማድረጉም ባለፈ፣ የሕዝብን አስተያየት በመሰብሰብ ለችግሮች መፍትሔ እንዲፈለግ ድልድይ ሆኖ ማገልገሉን ክብርት ወ/ሮ ፀሐይ ገልጸዋል። ይህ የተሳለጠ ተቋማዊ አሠራር እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ወጥ በሆነ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ የሺዋስ አለሙ በበኩላቸው፣ ባለፉት ስድስት ወራት የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ወደ 12 ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል። ከቁጥር መብዛት ባለፈም የይዘቶችን ጥራት ለማረጋገጥ የማያቋርጥ የክትትልና የግብረ-መልስ ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፣ በታችኛው መዋቅር የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን ለመሙላትና አሠራሩን ወጥ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በስፋት ተሰጥተዋል። ተቋሙ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን በቅንጅት በማሰለፍ፣ ዓላማ ተኮር የሆኑ ይዘቶች እንዲመረቱ በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንም ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው የታዩ ጠንካራ አፈፃፀሞችን በማጠናከርና ክፍተቶችን በማረም፣ የመረጃ ተደራሽነት ሥራው ይበልጥ እንዲዘምንና በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች የተናበበ ሥራ እንዲሠሩ አሳስቧል።
በጌታሁን ግርማ
