የልማት ክፍተቶችን ለመፍታት በተሰሩ ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ :- ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በምዕራብ ኦሞ ዞን የባቹማ ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

በምረቃው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹ፤ በክልሉ በመንግሥትና ፓርቲው መሪነት ባለፉት ዓመታት የልማት ውስንነት ባለባቸው አከባቢዎች የልማት ክፍተቶችን በመፍታት ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ፍትሃዊ የልማት ሥርጭት ባልተካሄደባቸው አከባቢዎች በፍትሃዊነት አዳዲስ በማስጀመርና ተጀምረው የቆሙትን በማጠናቀቅ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እየተቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም ምዕራብ ኦሞ ዞን የልማት ክፍተት በሰፊው የሚታይበት አከባቢ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።

በአከባቢው የሚታየውን የልማት ክፍቱት ለመፍታት ከክልሉ መንግስት በጀት በተጨማሪ መንግስታዊ ባልሆኑ የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የትምህርት ቤት ግንባታ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

የባቹማ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ መመረቅ በአከባቢው ያለው ወጣት ኃይል ከንድፈ ሐሳብ ትምህርት ባሻገር በተግባራዊ ክህሎት እንዲበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው፣ የኮሌጁ መመረቅ በዞኑ በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አከባቢዎች የሚታየውን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ፣ ለአካባቢው ኢኮኖሚ መነቃቃትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በመርሐግብሩ የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *