6 ሺህ ሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቻይት ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት በምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ የተገነባው የቻይት ንጹህ መጠጥ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ።

የቻይት ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ ሲሆን 6ሺህ የአከባቢ ሕብረተሰብ ክፍሎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል።

በምረቃዉ ወቅት የክልሉ ውሃ ማዕድና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው እንደገለጹት ፤ ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ከ490 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ብለዋል።

በዚህም የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ህዝብ ቁጥር 1.8 ሚሊዮን ደርሷል ያሉት ኢንጂነሩ ይህም የክልሉ መንግስት ለመሰረተ ልማት መስፋፋት የሰጠዉ ትልቅ ትኩረት ውጤት ነው ብለዋል።

የቻይት ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከ15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መገንባቱን ጠቅሰዉ አጠቃላይ 6 ሺህ የአከባቢ ሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው የገለፁት።

የንጹህ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታው 202 ሜትር ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የ100 ሜትር ኩብ የኮንክሪት የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ግንባታ፣ ከ4 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የፓምፕና የጄነሬተር አቅርቦት፣ ተከላ እንዲሁም የቤት ግንባታ እና 6 የውሃ ቦኖዎች ግንባታና ሌሎችን ያከተተ ነው ብለዋል።

ተገንብተው የተመረቀው የቻይት የንጹህ መጠጦ የውሃ ፕሮጀክት እንግልትን የሚቀንስ፣ የህጻናትን ጤንነት የሚጠብቅና የአካባቢውን ልማት የሚያፋጥን መሆኑን ገልጸው የፕሮጀክቱ ዘላቂነትና ተገቢው አገልግሎት እንዳረጋገጥ 6 የውሃ ተጠቃሚ ማህበራት ተደራጅተው ተቋሙን እንዲያስተዳድሩ አስፈላጊው ስልጠና መሰጠቱንም ተናግረዋል።

በተያያዘም ዜና የክልሉ የአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት ማሻሻያ ፕሮጀክት የተገነባ የማጂ እንስሳት ጤና ኬላ ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *