የአድዋ ድል የአብሮነት፣ የአንድነትና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነ አሰባሳቢ ታሪካችን ነው:- አቶ ቀጀላ መርዳሳ

Spread the love

የአድዋ ድል የአብሮነት፣ የአንድነትና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነ አሰባሳቢ ታሪካችን ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን 128ኛውን የአድዋ በዓልን “አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ አክብሯል።

የመታሰቢያ በዓሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ፣የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ፣ የተቋሙ ሰራተኞችና አባት አርበኞች በተገኙበት በተለያዩ መርኃ ግብሮች ተከብሯል።

በመድረኩ የአድዋ ድልን የሚተርኩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በዓሉን የተመለከቱ ትርኢቶችም ቀርበዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት አሁን ላይ የአድዋ ድል በዓል ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

የአድዋ ድልን የአብሮነት፣ የአንድነትና የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነ አሰባሳቢ ታሪካችን ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ለአንድ አላማ በአንድ ልብ በጋራ በመሰለፍ የአገራቸውን ነፃነት ያስከበሩበት ድል መሆኑን በማስታወስ ድሉም ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ችቦ እና ዓርማ መሆን እንደቻለ አስረድተዋል።

የአሁኑ ትውልድ አባቶቻችን በአድዋ የሰሩትን ታሪክ ድህነትን በተግባር በመታገልና የራሱን ታሪክ በመስራት ሊደግመው ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አባቶቻችን በአድዋ የሰሩትን ታሪክ ለመድገም የአሁኑ ትውልድ በአንድነት ተባብሮ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው አድዋ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተውና በጋራ በመቆም አንፀባራቂ ድል የተቀዳጁበት ነው ብለዋል።

የአድዋ ድልን ባህላዊ እሴቶቻችንን መሰረት በማድረግ የችግሮቻችን መፍቻ መንገድ ልናደርገው እንደሚገባ በመጠቆም ድሉን ለዘላቂ ልማት ልናውለው ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።

ድሉን አባቶቻችን በአድዋ የሰሩትን ተጋድሎ በማስታወስና በመዘከር እንዲሁም ትውልዱን በሚያስተምር መልኩና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ ልናከብረው ይገባል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ለተጨማሪ መረጃዎች በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተላሉን 👇

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *