






የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ55 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባውን ዘመናዊ የኢ-ኮሜርስ ሎጂስቲክስ ማዕከል በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
አየር መንገዱ በዛሬው ዕለት ያስመረቀው መሠረተ ልማት በአፍሪካ በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
በልዩ ሁኔታ ለኢኮሜርስ ሸቀጦች እንዲሁም ለፖስታ እና ጥቅል መልእክቶች የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ ወደ ስራ የሚገባው መሰረተ-ልማት፤ የአፍሪካን የኢኮሜርስ ኢንደስትሪ ዕድገት ከማፋጠኑም ባሻገር፣ አዲስ አበባን በአፍሪካ ብሎም በዓለም የድንብር ተሻጋሪ ኢኮሜርስ ማዕከል የሚያደርግ መሆኑን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ፣ የትራንሰፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
ዶ/ር አለሙ ስሜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስገነባው የኢ-ኮሜርስ ሎጂስቲክስ ማዕከል መንግስት ለሀገራዊ እድገትና ብልጽግና የያዘውን ስትራቴጂ ራዕይ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓት የሚገዙ እቃዎችን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር መኖሩን ገልፀው፤ በኢትዮጵያ የገበያ ትስስሩ ይበልጥ ማደግ ይገበዋል ብለዋል።
ዶ/ር በለጠ ሞላ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከሌላው ዓለም ሀገራት የሚያገናኝ ነው ብለው፤ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በቅንጂት እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበሩን ገልጸው፤ የዲጂታል ግብይት በዓለም ደረጃ እያደገ በመምጣቱ የመደበኛው ካርጎ አገልግሎት እየቀነሰ እና የኢ-ኮሜርስ አገልግሎት እየሰፋ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ አየር መንገዱ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አየር መንገድ ገቢው ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሰበሰበው ከካርጎ አገልግሎት መሆኑን በመጥቀስ የዘርፉን አቅም ይበልጥ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2023 ምርጥ የካርጎና ሎጅስቲክስ ኦፕሬተርና የአፍሪካ ምርጡ የካርጎ ኦፕሬተር በሚል በሁለት ዘርፎች ለአምስተኛ ጊዜ መሸለሙን ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
