የካራማራ ድል የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ዋጋ የተከፈለበት ታላቅ ድል ነው

Spread the love

የካራማራ ድል የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ዋጋ የተከፈለበት ታላቅ ድል መሆኑን የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት ገለጹ።

የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በመነጠል ታላቋን ሶማሊያ መመስረት በሚል ዚያድ ባሬ በ1969 ዓ.ም መጠነ ሰፊ ወረራ ማድረጉ ይታወቃል።

የሶማሊያ ወታደሮች በወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ መሪነት በምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትር ዘልቀው በመግባት ወረራ በፈፀሙ ጊዜ ኢትዮጵያውያን የጠላትን ሃይል በመፋለም ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋገሩ።

የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ደግሞ የሶማሊያን ወራሪ ሃይል በመደምሰስ ካራማራን ነፃ ያወጡበት ታላቅና ታሪካዊ የድል ቀን ነው።

ከ1950ዎቹ መባቻ ጀምሮ የፖሊስ ሠራዊትን ተቀላቅለው ሀገራቸውን ለበርካታ አሥርት ዓመታት ያገለገሉት ብርጋዴር ጄኔራል አንዳርጌ መሸሻ፤ የሶማሊያ ጦር በ1956 ለመጀመሪያ ጊዜ ትንኮሳ በፈፀመበት ወቅት ትንኮሳውን የቀለበሰው የምስራቅ ኢትዮጵያ የፖሊስ ሠራዊት አስተባባሪ ነበሩ።

የሀገር ባለውለታ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል አንዳርጌ፤ የካራማራን ድል በሚመለከት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ድሉ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በጀግንነት የተከፈለ መስዋዕትነት መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት የማይደራደሩ መሆናቸውን በተግባር ካረጋገጡባቸው ታሪካዊ ሁነቶች መካከል ካራማራ አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ክብርና ጀግንነት እስካሁንም መዝለቁን የገለጹት ብርጋዴር ጄኔራሉ፤ ከሀገር አልፎ የአፍሪካ የሰላም ዘብ በመሆኑ የሁላችንም ኩራት ነው ብለዋል።

በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ሀገራቸውን በአርበኝነት ያገለገሉትና በ1969 ዓ.ም በሶማሊያ ወረራ ወቅት የዘመቱት ኮሎኔል ጃል ዑመር፤ የካራማራ ድል ኢትዮጵያውያን ለወራሪ ኃይል መቼም ቢሆን እንደማይንበረከኩ ያረጋገጡበት መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት በመዳፈር ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት የነበረውን የጥፋት ትልም ያከሸፈ ታላቅ ድል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የካቲት 26 ቀን 1970ዓ.ም የኢትዮጵያ ጀግኖች ወራሪው የዚያድባሬ ጦር ካራማራ ላይ ድል ያደረጉበትና የኢትዮጵያ አሸናፊነት የታወጀበት ታሪካዊ እለት ዘንድሮ 46ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *