ኢትዮጵያ ታሪካዊ ስብራቶቿን እየጠገነች ወደ ወርቃማው ምዕራፍ እየተሸጋገረች ትገኛለች፦አቶ አለማየሁ አለሙ

Spread the love

በሸካ ዞን የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሃግብር በድምቀት እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሃግብሩ ላይ የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ታሪካዊ ስብራቶቿን እየጠገነችና እምቅ ሀብቷን በመጠቀም ወደ ወርቃማው ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኑን ገልፀዋል።

​በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁመና እየተቀየረ ከመሆኑም ባለፈ በብዙ ዘርፎች ራሷን የመቻል እቅዷን እያሳካች ትገኛለች ብለዋል አቶ አለማየሁ።

ሀገር በምክክርና በሽግግር ሂደት ቁስሏን እያከመች፣ ነገዋን እየተለመች ትገኛለች ያሉት አቶ አለማየሁ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጉዞ ውጤት እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

​ይህን ውጤታማ ጉዞ ለማስቀጠል ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው ​የፓርቲው ዋነኛ መርህ “ትናንትን ማከም፣ ነገን መተለም” መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክና ሰፊ አቅም ቢኖራትም፣ ላለፉት ዓመታት እንደ እድሜዋና እንደ አቅሟ ማደግ እንዳልቻለች አስታውሰዋል።

​መሻሻል ሲገባቸው ወደኋላ የቀሩ አሰራሮች፣​መፈታት ሲገባቸው ውሎ ያደሩ ችግሮች፣​ሀገሪቱን ቀፍድደው የያዙ መሰረታዊ ችግሮችንና ሌሎችን ጉዳዮች ​ብልፅግና ፓርቲ በመፍታት የኢትዮጵያን ነገ ብሩህ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን እምቅ አቅም ወደ ኢንዱስትሪ በመለወጥና ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ለማረጋገጥ ፓርቲው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የ7ኛው ሀገራዊ የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ሲሆን፣ ምልክቱ የመደመር፣ የአንድነት እና የትብብር ተምሳሌት ነው ያሉት አቶ አለማየሁ ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *