


በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት አዘጋጅነት የገቢ ተቋም ፈፃሚዎች አገልግሎት አሰጣጥና ሥነ ምግባር ችግሮችን ለመፍታት ከንግድ ማህበረሰብ ጋር የምክክር መድረክ በቴፒ ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት በላይ በወቅቱ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ቴፒ ከተማ የራሱን የወጪ ፍላጎት በራሱ ገቢ መሸፈን የቻለ ቢሆንም ፣ ያለውን አቅም ሙሉ በሙሉ መጠቀም አልተቻለምና ከዚህ በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደሚቻል ነው የተናገሩት።
በገቢ ተቋማት የሚታዩ የሥነ-ምግባርና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን በመቅረፍ ለውጤታማ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በትኩርት መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
ከተማውን ለማሳደግ የንግዱ ማህበረሰብ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም ወ/ሮ ትዕግስት አክለዋል።
የሸካ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ በላቸው በቀለ እንደገለፁት የአንድ ሀገር እድገትና ልማት የሚወሰነው ጤናማ የሆነ የግብር አሰባሰብ ስኖር ነው ብለዋል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያስችል የግብዓት ማሰባሰብያና በየደረጃው የሚገኙ የገቢ ተቋማት ፈፃሚዎች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የሥነ-ምግባር ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የቴፒ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገላቲያስ ሻሜ በበኩላቸው በከተማው ውስጥ ከ13ሺ በላይ ነጋዴዎች እንዳሉ ገልፀው ማናቸውም ለሚነሱ ጥያቄዎች የከተማ አስተዳደሩ ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
በመመሪያው መሰረት የደረጃ ሽግግር ለማድረግ ፍቃደኛ ያለመሆን ፣በህገወጥ መንገድ ለመነገድ
ፍላጎት መኖር ሽያጭን ያለደረሰኝ መፈፀምና የህግ ተጠያቂነትን ያለመፍራት በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን የቴፒ ከተማ ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰውነት እንደሻው ገልፀዋል።
አስተያየት ከሰጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ የደረጃ ሽግግርና የግብር ተመን በፍትሐዊነት አቅምን ያመጣጠነ እንዳልሆነ አንሰተው ፈጻሚው አካል የግንዛቤ ችግር ያለበትን ግብር ከፋይ በስርዓት አስረድቶ ያለማስተናገድ ችግር እንዳለም ተናግረዋል።
ለህገወጥ ነጋዴዎች ከለላ የሚሰጡ የፍፃሚ አካላት እንዳሉም አስረድተዋል።
በተቋም ፈፃሚዎች አገልግሎት አሰጣጥና ስነ ምግባር ችግሮች ላይ የንግዱ ማህበረሰብ በስፋት ሀሳባቸውን አንስተዋል።
በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያና ምላሽ ከሚመለከታቸው አካላት ተሰጥቶባቸው መድረኩ ተጠናቋል ሲል የዘገበው ማሻ ኤፍ ኤም ነው።
