የቦንጋ ዶሮ ዕርባታ ማዕከል በአገር ውስጥ የተባዛ ቴትራ ኤች የተሰኘ የዶሮ ዝርያ እንቁላል በማስፈልፈል የመጀመሪያ ዙር የአንድ ቀን ጫጩቶችን ማሰራጨት ጀመረ።

Spread the love

‎የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቦንጋ ዶሮ ዕርባታ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ለገሠ ሻሮ እንደተናገሩት፣ማዕከሉ በምርታማነታቸው የተሻለ ውጤት የሚያስገኙ የዶሮ ዝርያዎችን በጥናት በመለየት የተጠቃሚውን ማህበረሰብ ፍላጐት የማሟላት ተግባር እያከናወነ ይገኛል።

‎ለስጋና እንቁላል የሚሆኑ ቴትራ የተሰኙ ምርጥ የዶሮ ዝሪያዎችን ለክልሉ ሁሉም ዞኖች ለማሰራጨት በተደረገው የቅድመ ዝግጅት ስራ የክልሉ መንግሥት ወደ 60 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የማዕከሉን መሠረተ ልማት የማሟላት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

‎በዚህም 12 ሚሊዮን ብር በሆነ ውጪ 12 ሺህ የሚሆኑ ወላጅ ዶሮዎችን (parent stock) ወደ ማዕከሉ በማስገባትና ክትትል በማድረግ አሁን ጫጩት የማስፈልፈል ተግባር መጀመሩን አስረድተዋል።

‎የማዕከሉን ጫጩት የማስፈልፈል አቅም ለማሳደግ እንዲቻል ጫጩት ለማስፈልፈል የሚያሰችል ማሽን ለመጨመር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ እና በአሁኑ ሰዓት በአንድ ጊዜ አስከ 10ሺህ በማስገባት በአራትና አምስት ቀናት ልዩነት እስከ ዘጠኝ ሺህ ቴትራ የተሰኙ የዶሮ ጫጩቶችን ለማስፈልፈል መቻሉን አቶ ለገሠ ገልጸዋል።

‎በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ 7ሺህ ጫጩቶችን ለማሰራጨት እንደተቻለም አውስተው ‎ዶሮዎቹ በሽታ ከመቋቋምና ቶሎ ከማደግ ባሻገር ለእንቁላል እና ለስጋ ተመራጭ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ለገሠ ይህ በተጠቃሚው ማህበረሰብ ዘንድ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር በመቅረፍ ለክልሉ ሁሉም ዞኖችና አጎራባች ክልሎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሰራጨት የሚያስችል እንደሆነም አክለዋል።

‎ማዕከሉ በመኖ ማቀነባበሪያም ሆነ ጫጩት በማስፈልፈል ረገድ የተሻለ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው በዶሮ ሀብት ልማት ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት የአንድ ቀን ጫጬት ለ48 ቀን ከሚያገለግል መኖ ጋር አስፈላጊው ክትባት ተሰጥቿቸው በተመጣጠኝ ዋጋ መመቻቸታቸውንም አስገንዝበዋል።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *