


መንግሥት ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።
8ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና ፀጥታ የጋራ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የሰላም ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት ይህ የምክክር መድረክ “ሰላማዊ ፖለቲካ ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በወቅታዊ ሀገራዊ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት እና የልምድ ልውውጥ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።
በፌዴራል እና በክልል የሰላምና የፀጥታ ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅት፣ ተግባራዊ ትብብር እና የጋራ መግባባት ይበልጥ ማጠናከርም ሌላኛው የመድረኩ ዓላማ መሆኑ ተመላክቷል።
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲስ አበባ ሰላምና ልማት የተረጋገጠባት የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል እየሆነች የመጣች ከተማ ናት ብለዋል።
በአመራሩና በሕዝብ ቅንጅት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች መዲናዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ሕዝብን በባለቤትነት በማሳተፍና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተከናወነው ውጤታማ የሠላም ሥራ ለሌሎች አካባቢዎችም በተምሳሌትነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ለውጡ የመዲናዋንና የሀገርን ዕድገት በማፋጠን ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ አስደናቂ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ብለዋል።
መንግሥት በመደመር መንገድ እየተመራ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳካት እየተጋ መሆኑን አረጋግጠዋል።
መንግሥት የሰላም በርን ለሁሉም ክፍት ማድረጉን ያነሱት ሚኒስትሩ በዚህም በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውንና የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አሁንም የሰላም ጥሪውን ያልተቀበሉ አካላት የሰላም አማራጭን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የዘመናት ስብራትን ለመጠገን አመርቂ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሰላምና ጸጥታ መዋቅሩ አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኩል የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጡም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የክልል ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ አመራሮች ተገኝተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
