




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ 2018 ግማሽ ዓመት የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም ላይ ከተገልጋይ፣ ከህዝብና ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እያካኸደ ነው።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግግር ያደረጉት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ከታችኞቹ ተቋማት የጀመረው ይህ መድረክ በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግብዓት መሰብሰብ የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጠዋል።
በክልሉ ባሉት ፍርድ ቤቶች ለተገልጋዩ ፍትሐዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የፍትህ ተቋማት መቀናጀት ለተፈለገው ውጤት ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
ከዚህ ምክክር መድረክ የሚገኙ ግብዓቶችና ከአፈጻጸም ሪፖርቱ የሚገኙ ነጥቦችን በትኩረት ለይተው የህዝባችንን የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች መፍታትና እርካታቸውን መጨመር ይጠበቃል ብለዋል
በመድረኩ የመክፈቻው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም: የዳኝነት ተቋማት ህግና ህገ-መንግስታዊነትን የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለው በመገንዘብ አግልግሎት እየሰጠ እንዳለ ገልጸዋል።
መንግስት የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ የፍርድ ቤቶች የሪፎርም ካርታ አዘጋጅተው ተግባራዊ በማድረግ ከዚህ ቀደም የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራር ችግሮች እያስቀረ መጥተዋል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር የዳኝነት ተቋማት አደረጃጀቶችን መልሶ በማየት በክልሉ በሁሉም የዳኝነት ተቋማት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እያስከበሩ ግለሰባዊና ተቋማዊ የዳኝነት አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ 6 ወራት በ29 ሺህ 379 ወንጀልና ፍትሐብሔር መዝገቦች ላይ ቀልጣፋና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎትን ለመስጠት ታቅደው 24 ሺህ 748 መዝገቦች ላይ እልባት በመስጠት የዕቅዱን 84 በመቶ ማከናወን መቻሉን ገልጿል።
በመድረኩ ላይ የክልሉና የዞኖች የመንግስት ስራ ኃላፎዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የአፈጻጸም ሪፖርት እየቀረበ ይገኛል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
